ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ ተኪ ምርት ተመረተ

አርባ ምንጭ፤ ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፡- በ2018 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ ተኪ ምርት መመረቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ የ2018 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ አፈጻጸም ተጠሪ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአርባ ምንጭ ከተማ እየተገመገመ ነው።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚሁወቅት፤ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሀገሪቱ ራሷን የምትችልበት የሉዓላዊነት ማጠንጠኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በዚህም ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ባለፉት ስድስት ወራት 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ ተኪ ምርት መመረቱን ገልጸው፤ 204 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ምርትም ወደ ውጭ ተልኳል ብለዋል።
 
በተጠናቀቀው ግማሽ የበጀት ዓመት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከ161 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ በዘርፉ በርካታ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ መቻሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲነቃቃ በማድረጉ የማምረት ዐቅም ባለፈው ዓመት ከነበረው ከ46 በመቶ ዘንድሮ ወደ 66 በመቶ አድጓል ነው ያሉት።

በሌሎች ሀገራት የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ መኖር አይቻልም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሀገሪቱን በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማበልጸግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በተኪ ምርት ላይ ትኩረት በማድረጋችን ፈጣን ለውጥ እየተመዘገበ ይገኛል፤ ይህም የኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን የሚያጠናክር ፖሊሲ ተቀርጾ ወደ ሥራ የመገባቱ ውጤት ነው ብለዋል።



 
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጌትነት በጋሻው (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ ከ2 ሺህ በላይ አነስተኛ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ ጠቅሰው ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።



 
መንግሥት ለኢንዱስትሪ ልማት በሰጠው ትኩረት የዜጎች ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ መምጣቱን የተናገሩት ደግም በብልጽግና ፓርቲ የአርባ ምንጭ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አይሶጸ ሂሎታ ናቸው።
 
በአካባቢው የሚገኙ የሞሪንጋ፣ ሙዝና የሸማ ምርቶች ላይ ዕሴት በመጨመር ተጠቃሚነትን ማሳደግ መቻሉንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም