ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ሀገራዊ የድርጊት መርሃ ግብር እያዘጋጀች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ሀገራዊ የድርጊት መርሃ ግብር እያዘጋጀች ነው
አዲስ አበባ፤ጥር 16/2018 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ሥርዓታዊ እና ሕጋዊ የፍልሰት አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ሀገራዊ የትግበራ ዕቅድ እያዘጋጀች መሆኗን የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ ገለጹ።
የዓለም አቀፉ የፍልሰት ስምምነት (Global Compact for Migration) ብሔራዊ የትግበራ ዕቅድ ዝግጅትን በተመለከተ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
እ.ኤ.አ. በ2018 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸደቀው ይህ ስምምነት ፍልሰተኞች ከሚነሱበት እስከ መድረሻቸው ድረስ መብታቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲኖር የሚያስችል የመጀመሪያው አጠቃላይ ማዕቀፍ ነው።
የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ የፍልሰት መነሻ፣ መሸጋገሪያና መድረሻ ሀገር በመሆኗ ለስምምነቱ መሳካት ቀደምት ተሳትፎ ስታደርግ መቆየቷን አስታውቀዋል።
እ.ኤ.አ. በ2020 ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የመጀመሪያዋ የስምምነቱ ሞዴል ሀገር በመሆን የመጀመሪያውን ሀገራዊ ሪፖርት ማቅረቧን ጠቅሰዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በክልላዊና ዓለም አቀፋዊ የስምምነቱ ግምገማ ሂደቶች ላይ በንቃት በመሳተፍ የተቀናጀ ትግበራን ለማስፈን በፌዴራልና በክልል ደረጃ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ስታከናውን መቆየቷን ተናግረዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሚመራ የመንግሥትና የማህበረሰብ ተሳትፎ ያለበት የቅንጅት መድረክ መቋቋሙን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ሀገራዊ የስደተኞች ፖሊሲ ተረቆ ለማፀደቅ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
አጠቃላይ ሀገራዊ የትግበራ ዕቅድ መዘጋጀቱ በፌዴራልና በክልል ደረጃ ያለውን የዓለም አቀፉ የፍልሰት ስምምነት ትግበራ ለማቀናጀትና ለማፋጠን ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ይህ ዕቅድ በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት መካከል ጠንካራ ትብብርን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ ሀገራዊ የትብብር ጥምረት ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) ጋር በመሆን ሂደቱን በሥርዓት፣ሁሉንም ባሳተፈ፣ጾታን ባገናዘበና ውጤት ተኮር በሆነ መልኩ ለመምራት የሚያስችል ዕቅድ መዘጋጀቱን አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ተወካይ አቢባቱ ዋኔ በበኩላቸው፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር ባለፉት ዓመታት የፍልሰት አስተዳደር ሥርዓትን ከኢጋድ እና ከዓለም አቀፍ መርሆዎች ጋር የማጣጣም ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
ይህ አዲስ እየተዘጋጀ ያለው ብሔራዊ የትግበራ ዕቅድም ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት ለፍልሰት ጉዳይ የሚሰጡ ግቦችን ለመለየት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚያሳየው ቁርጠኝነትና ባለሙያዎች ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።