ቀጥታ፡

ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ሆሳዕና፤ ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ገለፀ፡፡

በክልሉ የመንግሥት አገልግሎትና አሥተዳደር ሪፎርም ትግበራ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡


 

በዚሁ ወቅት የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ገብሬ ጋጌ እንዳሉት፤ የመንግሥት አገልግሎትና አሥተዳደር ሪፎርምን በመተግበር ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን እየተሠራ ነው።


 

ከዚህ በፊት በመንግሥት አገልግሎት ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል ፖሊሲን ከመቅረፅ ጀምሮ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሲነሱ የነበሩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራርን ከመተግበር አንጻር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወደ ሥራ መግባቱን አንስተዋል።

በክልሉ የመንግሥት አገልግሎትና አሥተዳደር ሪፎርም በጤና፣ በፋይናንስ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት እና በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ልማት ቢሮዎች ለመጀመሪያ ዙር ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

የሪፎርሙ መተግበር የአገልግሎት አቅርቦቱን ወጥነት ያለው እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር የተገልጋዩን እንግልት እንደሚቀንስ ገልጸው የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም