የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚያሳልጡና ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚያሳልጡና ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ነው
አዲስ አበባ፤ጥር 16/2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምሰሶዎችን ማሳለጥ ታሳቢ ያደረጉና ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ከኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ወጣቶች ችሎታቸውንና ሀሳባቸውን ትርጉም ወዳላቸው ፈጠራዎች መቀየር የሚችሉበት "ክህሎት ኢትዮጵያ" የተሰኘ መርሃ ግብር ተግባራዊ አድርጓል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም ሦስተኛውን ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር ባስጀመሩበት ወቅት፤ የክህሎት ኢትዮጵያ እሳቤ ወጣቶች የማህበረሰቡን አንገብጋቢ ፍላጎቶች እንዲመረምሩና ሀገራቸውን የሚጠቅሙ መፍትሔዎችን እንዲፈጥሩ የሚያስችል መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ በመደበኛና አጫጭር ሥልጠናዎች በዓመት እስከ ስድስት ሚሊዮን ዜጎች የማስተናገድ አቅም አለው፡፡
በ"ክህሎት ኢትዮጵያ" መርሃ ግብር ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ የፈጠራ ባለሙያዎች ግብዓት ተሟልቶላቸውና የፈጠራ ባለቤትነት መብታቸው ተጠብቆላቸው የፈጠራ ሀሳባቸውን እውን የሚያደርጉበት አቅም እየገነቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ወጣቶቹ በግልና በቡድን በመሆን ከ100 በላይ አዳዲስ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎችን ማውጣት ችለዋል ብለዋል፡፡
እነዚህ የፈጠራ ስራዎች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በትኩረት መስክነት የተለዩትን የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝም፣ የማዕድንና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎችን የተከተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረጉና ቀጣናዊ ትብብርን የሚያጠናክሩ እንደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ሳይበር ደህንነት፣ ባዮሜዲካል ቴክኖሎጂ፣ ሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ መሰል አዳዲስ የስልጠና መስኮችን ጀምሯል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት እንደሚል ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በትምህርት መስኩም ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ በመስጠት የውጭ ሀገር ዜጎች የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ክህሎት ድንበር ተሻጋሪ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢንስቲትዩቱ በየዓመቱ 250 ለሚሆኑ የጎረቤት ሀገራት ወጣቶች የነፃ ትምህርት እድል እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ይሄውም ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገቷና ልማቷ በትብብር ላይ የተመሰረተ የቀጣናውን ሀገራት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን በተግባር ያሳያል ብለዋል፡፡