የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምክክር የተሻለ አማራጭ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምክክር የተሻለ አማራጭ ነው
ሆሳዕና፤ ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፡- የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምክክር የተሻለ አማራጭ በመሆኑ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ ስኬታማነት የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።
የሲዳማ ክልል የሀገር ሽማግሌ የሆኑት ታደሰ ኮራ እንዳሉት፤ አብሮነትን በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምክክርን ባህል ማድረግ የተሻለ አማራጭ ነው።
ሀገራዊ ምክክር ዋና ዋና የማያግባቡ ችግሮችን ፈትቶ ሀገራዊ አንድነትን በማምጣት የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና እንዳለውም አስገንዝበዋል።
የሀላባ ዞን የሀገር ሽማግሌ ኢማም ኡልጫፎ አብዶ፤ ምክክርን ባህል ማድረግ ተቀራርቦ በመነጋገር የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር የጎላ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
ነፍጥን አንግቦ ጫካ በመግባት መፍትሔ እንደማይገኝ ጠቁመው፤ ተሰሚነታቸውን በመጠቀም ሀገራዊ አንድነትን ሊያጠናክሩ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በመሥራት የኮሚሽኑን ተግባር እያገዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሀገር ጉዳይ በጋራ መክሮ የወል እሳቤና ትርክት ለመያዝ በኮሚሽኑ የተጀመሩ አሳታፊና አካታች የምክክር ሥራዎች ፋይዳቸው የጎላ ነው ያሉት ደግሞ የሀድያ ዞን የሀገር ሽማግሌ ዳኛ ሰለሞን ኃይሌ ናቸው።
ለቆዩ ችግሮች ተቀራርቦ በመወያየት የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ምክክሩ መደላድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
ልማት እንዲጠናከርና ሀገራዊ ምክክሩም ውጤታማ እንዲሆን እንደ ሀገር ሽማግሌ ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስተያየት ሰጭዎቹ ለኢዜአ አረጋግጠዋል።