ቀጥታ፡

ማንችስተር ሲቲ ከዎልቭስ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ጥር 16/2018 (ኢዜአ):- የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ ይጀመራል።

በዕለቱ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ማንችስተር ሲቲ በኢትሃድ ስታዲየም ዎልቭስን ያስተናግዳል።

ማንችስተር ሲቲ በ43 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ዎልቭስ በስምንት ነጥብ የመጨረሻው 20ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ውሃ ሰማያዊዎቹ ባለፉት አራት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፉም። ከ12 ነጥብ ማግኘት የቻሉት ሶስት ብቻ ነው።

በአንጻሩ በሊጉ 16 ሽንፈት ያስተናገደው ዎልቭስ በበኩሉ በውድድር ዓመቱ አንድ ጨዋታ ብቻ ነው ማሸነፍ የቻለው።

ማንችስተር ሲቲ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት ከዛሬው ጨዋታ ሶስት ነጥብ መውሰድ ይኖርበታል።

ዎልቭስ ማሸነፍ ከከረመበት ወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ትግል አጋዥ አቅም ይሆነዋል።

በሌሎች መርሃ ግብሮች ቦርንማውዝ ከሊቨርፑል ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ በቫይታሊቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ቦርንማውዝ በ26 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል። ሊቨርፑል በ36 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ባለሜዳው ቦርንማውዝ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣ ሊቨርፑል ከአራት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።

ዌስትሃም ዩናይትድ ከሰንደርላንድ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30፣ ፉልሃም ከብራይተን እና በርንሌይ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም