ቀጥታ፡

በልማት ስራዎች ላይ በንቃት ከተሳተፍን በራስ አቅም ሀገርን መገንባት እንደምንችል ተገንዝበናል - ወጣቶች 

አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦በልማት ስራዎች ላይ በንቃት ከተሳተፍን  በራስ አቅም ሀገርን መገንባት እንደምንችል ተገንዝበናል ሲሉ ወጣቶች ገለፁ።

የፌዴራል ተቋማት ብልፅግና ፓርቲ የኢኮኖሚ ክላስተር ወጣቶች ክንፍ "የወጣቶች በጎ እይታ ለታላቋ ኢትዮጵያ " በሚል መሪ ሀሳብ የኤኤምጂ ኢዲአር የባቡር መስመር እና የእንዶዴን ደረቅ ወደብ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።


 

በጉብኝቱም ወቅት የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አክስዮን ማህበር የባቡር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ዘርፉን በማዘመን ለተጠቃሚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚከናውናቸውን ተግባራት የፕሮጀክቱ የስራ ሃላፊዎች ለጎብኚዎች ገለጻ አድርገውላቸዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ዋና ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ ገዛኸኝ አንዳርጌ  በዚሁ ወቅት እንደገለጸው፤ በመንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገርን ወደ እድገት የሚያሻግሩ  የልማት ስራዎችን እየተከናወኑ ይገኛል።

ወጣቶችም እነዚህን ተጨባጭ የልማት ስራዎች በማየት ነገ ለሀገራቸው የተሻለ ነገር ማበርከት እንዲችሉ ታስቦ የተዘጋጀ  መርሀ ግብር መሆኑንም ተናግሯል።


 

በኢትዮጵያዊያንና በሀገር ሀብት እየተሰሩ ያሉት የልማት ፕሮጀክቶችን መመልከት በወጣቶች ዘንድ ትልቅ ተስፋ የሚያጭር መሆኑን ገልጿል።

ይህም በቀጣይ ወጣቶች በሀገራቸው ልማት ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መነሳሳት የሚፈጥር ነው ብሏል።

በፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት የብልጽግና ወጣቶች ክንፍ የኢኮኖሚ ክላስተር ሰብሳቢ ወንድማገኝ ይርጋለም በበኩሉ፤ ሀገራችን በተለያዩ መስኮች የጀመረቻቸው የልማት ስራዎች ላይ የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል ወጣቱ ሀይል ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ በጉብኝታችን ተመልክተናል ብሏል።


 

በቀጣይም የሀገራችንን ብልፅግና በሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ላይ እንደ ወጣት የሚጠበቅብንን ማበርከት እንዳለብን የቤት ስራ ወስደናል ሲል ገልጿል።

ኑሪያ ሁሴን እና ትዕግስት ሽፈራው በበኩላቸው፤ የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር  አክስዮን ማህበር ለዜጎች ፈጣን እና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት በሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች ኩራት ተሰምቶናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም