ቀጥታ፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከልና የማከም ሥራ ውጤት እያስመዘገበ ነው - የጤና ሚኒስቴር    

አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦በሀገር አቀፍ ደረጃ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከልና የማከም ሥራ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ መምጣቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።  

የጤና ሚኒስቴር የብሔራዊ ''ፔን ፕላስ' (ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች) ሕክምና የድርጊት መርሀ ግብር ይፋ አድርጓል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቆጣጠርና መከላከል ተጨባጭ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኝ አስረድተዋል።


 

የሕክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት የጤና ተቋማትን ደረጃ ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎችም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመቀነስ አበረታች ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ከ2026 እስከ 2030 በሚቆየው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሕክምና የድርጊት መርሀ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ በ150 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች አገልግሎትን ማሳደግ እንደሚያስችል አስታውቀዋል።

ይህም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሕክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት በማስፋት ማህበረሰቡ በአቅራቢያው እንዲገለገል ያስችላል ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፤ ማህበረሰቡ ተላላፊ ያልሆኑ የበሽታ አይነቶችን ተጋላጭነትን ለመግታት የአመጋገብ ሥርዓቱን በማሻሻል የአካል ብቃት ማዘውተር ይኖርበታል ብለዋል። 


 

በቀጣይም የዜጎችን ተላላፊ ያልሆኑ የበሽታ አይነት ተጋላጭነት ለመቀነስ የሕክምና አገልግሎትን የማሻሻልና ግንዛቤ የማሳደግ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የስኳርና ደም ግፊት ተላላፊ ያልሆኑ የበሽታ አይነቶች እየጨመረ መምጣቱን ጥናቶች ያሳያሉ ያሉት ደግሞ በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ህይወት ሰለሞን ናቸው።


 

በዚህም ማህበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤውን በማሻሻልና ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ባህል በማድረግ ተላላፊ ያልሆኑ የበሽታ ሥርጭቶችን መቆጣጠር እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም