ቀጥታ፡

የእንስሳት ግጦሽ መሬት ደኅንነትን በማስጠበቅ የአርብቶ አደሮችን ዘላቂ ተጠቃሚነት የበለጠ ማረጋገጥ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦የእንስሳት ሃብት የግጦሽ መሬት ደኅንነትን በማስጠበቅ የአርብቶ አደሮችን ዘላቂ ተጠቃሚነት የበለጠ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አጉ ደባን ገለጹ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአውሮፓውያኑ 2026 የግጦሽ መሬትና አርብቶ አደርነት የማስተዋወቅ ዓመት እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል፡፡


 

የግብርና ሚኒስቴር፣ የመንግስታቱ ድርጅት፣ የዓለም አቀፍ የምግብና እርሻ ድርጅት እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ቀናት የሚቆይ "የግጦሽ መሬትና አርብቶ አደርነት ዓመት" ጉባኤ ማካሄድ ጀምረዋል።  

በጉባኤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አጉ ደባን እንደገለፁት፤ የግጦሽ መሬት ደኅንነትን በመጠበቅ የአርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት ማስቀጠል ያስፈልጋል።


 

አርብቶ አደሮች ከኋላቀር የእንስሳት ሃብት አስተዳደር በማላቀቅ አስተማማኝ የግጦሽ ምኅዳር ለመፍጠር ዘላቂ የተቋም አቅም መገንባት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ሚኒስትር ዴዔታ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ አማካሪ አለማየሁ መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የግጦሽ መሬት እንክብካቤና ጥበቃ ለአርብቶ አደር ማህበረሰብ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል። 


 

ኢትዮጵያም ሀገር በቀል የዳበሩ ዕውቀትና ልምዶችን በመጠቀም የአርብቶ አደሮችን የእንስሳት የግጦሽ መሬት ለመጠበቅ አበረታች ውጤት እያስመዘገበች መሆኗን ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ የግጦሽ መሬት ሥነ-ምኅዳር ጥበቃም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም የምግብ ዋስትናን በሚያረጋግጥ የአሰራር ሥርዓት የተደገፈ መሆኑን አስረድተዋል።

የአርብቶ አደሮች ፎረም መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ ሀጂ አብዲ አብዱላሂ ሀሰን፤ ጉባኤው የኢትዮጵያ የአርብቶ አደሮችን የእንስሳት ሃብት ተጠቃሚነት ለማሻሻል ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።


 

በተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ወርቂቾ ጃተኖ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮችን የግጦሽ መሬት ደኅንነት ለማረጋገጥ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ የአውሮፖ ሕብረት ፕሮጀክት ማናጀር ተሬሳ ጃለታ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ አርቦቶ አደሮችን ዘላቂ እንስሳት ግጦሽ መሬት አስተማማኝ ደኅንነት ለማስጠበቅ ይደግፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም