ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ያለ ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያውያን ባለቤትነት የሚመራ መሆኑ ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው

አዲስ አበባ፤ጥር 15 /2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ኢትዮጵያውያን በባለቤትነት የሚመሩት እና ከውጭ ጣልቃ ገብነት የጸዳ መሆኑ ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) ገለጹ።

አፍሪካውያን አለመግባባቶችን አፍሪካ መር በሆኑ መንገዶች ብቻ መፍታት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት 2014 ዓ.ም ጀምሮ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ የተሳታፊ ልየታ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎች ሲያከናውን ቆይቷል።

እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት መፍጠርን ዋንኛ ራዕዩ ያደረገው ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ ፣በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ፣ ምክረ ሀሳቦችን በማቅረብ እና ለተግባራዊነቱም የመከታተያ ስርዓት በመዘርጋት ለሀገራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ የግጭት እና የአለመግባባት መሰረታዊ መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በምክክር መፍታት መሆኑን ገልጸዋል።

የምክክር ሂደቱ ሀገር አቀፍ እና ዜጎችን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም የኢትዮጵያን ማህበራዊ መስተጋብር በግልጽ ውይይት፣በጋራ መከባበር እና በጋራ እውነትን በመፈለግ በድጋሚ ለመገንባት የሚያስችል ነው ብለዋል።

ምክክሩ ከጊዜያዊ ጉዳዮች ይልቅ ለግጭት መንስኤ የሆኑ መዋቅራዊ ጉዳዮችን መፍታትን ያለመ መሆኑን ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።

የኢትዮጵያ የምክክር ሂደት በኢትዮጵያውያን ባለቤትነት የሚመራ መሆኑ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ የውጭ ቁጥጥር እና የውስን ግለሰቦች አጀንዳ ተኮር ሆነው ከተካሄዱ ብሄራዊ ምክክሮች እንደሚለየው ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ ሀገራዊ ምክክሩ ለቀጣናዊ መረጋጋት አዎንታዊ አንድምታ እንዳለው ያነሱ ሲሆን ውስጣዊ ጥንካሬ ቀጣናዊ ትብብር፣የንግድ ትስስር እና በጋራ መልማትን እንደሚያጎለብት ነው ያብራሩት።

በአፍሪካ ያሉ ችግሮች አፍሪካ መር በሆኑ ስርዓቶች ብቻ መፈታት እና በጋራ አህጉራዊ እሴቶች መመራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

አፍሪካውያን አለመግባባቶችን በትብብር መንፈስ ለመፍታት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም