ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ፈጣን እድገት ለአፍሪካ ሀገራት አብነት ይሆናል - የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች

አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር ኃይል ፈጣን እድገት ለአፍሪካ ሀገራት አብነት ይሆናል ሲሉ የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት ክብረ በዓልን በማስመልከት የተዘጋጀው የአቪዬሽን ኤክስፖ ተከፍቷል።


 

ኤክስፖው የወደፊቱን የአቪዬሽን አቅም በጋራ እንገንባ በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ኤክስፖውን የጎበኙ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች፤ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ በሚሆን አግባብ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ስለመሆኑ መታዘባቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የቦትስዋና ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ኮሎኔል ሞታሲ ቼሌኒያኔ፤ የኢትዮጵያ አየር ሃይል በአቪዬሽን፣ ኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አስደማሚ ለውጥ ውስጥ መሆኑን ከኤክስፖው መመልከታቸውን ገልጸዋል። 


 

በተለይ አየር ኃይሉን ጥገናን ጨምሮ በሌሎች ቁልፍ የዘርፉ ምህንድስና ስራዎች ራሱን ለመቻል እያከናወነ ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑን አንስተው፤ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከዚህ ልምድ መውሰድ እንዳለባቸው ተናግረዋል።  

በኢትዮጵያ የናሚቢያ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ማካንዚ ቺቤራ በበኩላቸው እንደገለጹት፤  ባለፉት ጊዜያትም ሆነ አሁን ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የራሱን እና የአፍሪካን አቅም ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ነው።


 

የአፍሪካ ሀገራት በጋራ እና በትብብር ከሰሩ ብዙ ርቀት መሄድ እንደሚችሉ ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አየር ሃይል የወሰደውን ተነሳሽነት አድንቀዋል።  


 

በኢትዮጵያ የጋቦን ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ኮሎኔል አርሲዴ አንጉሌ፤ የኢትዮጵያ አየር ሃይል  ሀገር የሚወክል ተቋም እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።  ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ጥሩ ምሳሌ ነው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም