የአዲስ አበባ የልማት ስኬቶች ለትውልድ የሚተላለፉ ናቸው-የአፋሕድ አመራር አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ የልማት ስኬቶች ለትውልድ የሚተላለፉ ናቸው-የአፋሕድ አመራር አባላት
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ የልማት ስኬቶች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ለትውልድ የሚተላለፉ መሆናቸውን የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) አመራር አባላት ገለጹ።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ከፍተኛ አመራር አባላት በአዲስ አበባ ከተማ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻና ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) የውጭ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ፤ አዲስ አበባን ለማስዋብ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ለትውልድ የሚተላለፉ ናቸው ብለዋል።
በኮሪደርና መዝናኛ፣ በወንዝ ዳርቻና ቅርስ ጥበቃ ልማት የተመዘገቡ ስኬቶች መዲናዋን ዓለም አቀፍ ውብ ገፅታ በማጎናጸፍ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በቅርስና ታሪካዊ ሥፍራ ጥበቃ የልማት ሥራ ላይ የተመዘገቡ ስኬቶች ቀጣዩን ትውልድ በሚቀርጽ የአሰራር ሥርዓት ተውበው የተገነቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
መዲናዋን በማስዋብ ሂደት ድጋፍና አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፌዴራል መንግስት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ባለድርሻ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ኢትዮጵያ በታሪካዊ ጠላቶች ፊት አውራሪነት በግጭት እንድትቆይ የተሸረበውን ሴራ በማጤን የሰላም አማራጭ እንደተቀበለ ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ላለፉት ዓመታት የተከሰተው ግጭትም ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው በማስተጓጎልና የመሠረተ ልማት ግንባታን በማቋረጥ እንቅፋት መፍጠሩን አስታውሰዋል።
በስምምነቱ መሠረትም በጫካ የነበሩት ወደ ተዘጋጀላቸው ጊዜያዊ ማዕከል በማሰባሰብ የህዝብ ሰላምና የልማት አካል ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።
የመዲናዋ የልማት ስኬቶች ጉብኝት ኃላፊነት የወሰድንበት ነው ያሉት ካፒቴን ማስረሻ፤ በቀጣይም የአማራ ክልልን የመሰረተ ልማት ሥራ ለማስቀጠል እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ወታደራዊ አስተዳደር ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር እያሱ አባተ፤ በመዲናዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ አስደናቂ የልማት ስኬት ተመዝግቧል ብለዋል።
የአዲስ አበባ የልማት ስኬቶችም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረጋቸውን በጉብኝታቸው እንዳረጋገጡ አስረድተዋል።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) አመራርና አባላት የሰላም አማራጭን መቀበል ለቀጣይ ሀገራዊ ልማትና ለህዝብ ተጠቃሚነት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) የስልጠና መምሪያ ኃላፊ መልካሙ ጣሴ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል ብለዋል።
በተለይም በሰው ተኮር ልማት የተገነቡ ፕሮጀክቶች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) መካከል የተደረገውን የዘላቂ ሰላም ስምምነት ማዕቀፍ ውጤታማ ለማድረግ የማስፈፀሚያ ስምምነት ትናንት ተፈርሟል።
በዚህም የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ወታደራዊ አስተዳደር መምሪያ ሃላፊ እያሱ አባተ (ረዳት ፕሮፌሰር) ስምምነቱን መፈረማቸው ይታወቃል።