የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ሥራችንን ለማዘመንና ለማቀላጠፍ አግዞናል -ሰልጣኞች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ሥራችንን ለማዘመንና ለማቀላጠፍ አግዞናል -ሰልጣኞች
ወልቂጤ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮ-ኮደርስ ያገኙት ስልጠና የዲጂታል ክህሎታቸውን በማሳደግ ሥራቸውን ለማዘመንና ለማቀላጠፍ እንዳገዛቸው በወልቂጤ ከተማ የኮደርስ ሰልጣኞች ገለጹ።
መንግስት ለዜጎች ያመቻቸው የአምስት ሚሊዮን የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና ዜጎች ከዲጂታል ዓለሙ ጋር ለመራመድ የሚያስችላቸውን የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት እያስጨበጣቸው ነው።
በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ ሠራተኞችም ስልጠናውን እንዲወስዱ በአስተዳደሩ የተመቻቸላቸውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የዲጂታል እውቀታቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ስልጠናውን የወሰዱት ሠራተኞች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮ-ኮደርስ በተለያዩ ዘርፎች ያገኙት ስልጠና የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማሳደግ ሥራቸውን እንዲያዘምኑና ውጤታማ እንዲሆኑ እያገዛቸው ነው።
በወልቂጤ ከተማ የኢንተርፕራይዝና ሥራ ዕድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት ባለሙያ ወጣት ሰለሞን ደርብ በኢትዮ ኮደርስ በዳታ ፕሮግራሚንግ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በአንድሮይድ ዘርፎች ስልጠና ወስዶ ክህሎቱን ማሳደጉን ተናግሯል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በሌሎች ዘርፎች ተጨማሪ ስልጠና እየወሰደ መሆኑን ጠቁሞ፣ በኮደርስ ስልጠና ባገኘው እውቀት በትርፍ ሰአቱ ተጨማሪ ሥራ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግሯል።
የከተማው ሳይንስ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽህፈት ቤት ባለሙያ ወጣት ጅብሪል መጀል በበኩሉ፤ የዲጂታል እውቀቱን ለማሳደግ የሚያግዘውን የኮደርስ ስልጠና በመውሰድ ከራሱ ባለፈ ሌሎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግሯል።
ያገኘው ስልጠና በኮምፒውተር ሳይንስ በዲግሪ ለመማር መነሳሳት እንደፈጠረለት ገልጾ፣ በቀጣይም በተለያዩ ዘርፎች የሚሰጠውን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መውሰዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።
በማይክሮ ሶፍት መተግበሪያዎች በወሰደው ስልጠና ያገኘውን እውቀትና ክህሎት በተቋም ሥራ በመተግበር ሥራውን ለማቀላጠፍና ለችግር መፍቻነት እየተጠቀመበት መሆኑን ተናግሯል።
በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ያለንን እውቀትና ክህሎት በማሳደግ ከዲጂታል ዓለም ፈጣን እድገት ጋር ለመጓዝ የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ ሰልጣኝ ወይዘሮ አቻምየለሽ ዘርጋ ናቸው።
ስልጠናው ከኋላቀር የመረጃ አያያዝ ስርዓት በማላቀቅ የግልና የመስሪያ ቤት መረጃዎችን ለማዘመን የሚያስችል እውቀት እንዳገኙበት ተናግረዋል፡፡
በኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና በአራት የተለያዩ ዘርፎች የቀሰሙት እውቀት በቴክኖሎጂ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያ እንዳደረጋቸው የተናገሩት ደግሞ የከተማው ንግድና ገበያ ልማት ባለሙያ አቶ ጅላሉ ሙዘይን ናቸው ።
ስልጠናው የተለያዩ አገልግሎት የሚሠጡ ሶፍትዌሮችን አበልጽገው እንዲጠቀሙ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሃምዱ ካሚል፤ በከተማው እስካሁን ድረስ 20ሺህ የሚጠጉ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወስደው የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ ስልጠናውን በሁሉም የመንግስት መዋቅር ተደራሽ በማድረግ ዜጎች የቴክኖሎጂ ክህሎትና ዕውቀታቸውን ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።