የጉምሩክ አገልግሎት ምኅዳር የመድኃኒትና ሕክምና መሳሪያ አምራቾችን ምርታማነት እያጎለበተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጉምሩክ አገልግሎት ምኅዳር የመድኃኒትና ሕክምና መሳሪያ አምራቾችን ምርታማነት እያጎለበተ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦የጉምሩክ አገልግሎት ምኅዳር የሀገር ውስጥ የመድኃኒትና ሕክምና መገልገያ መሳሪያ አምራቾችን ምርታማነት እያጎለበተ መሆኑን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን እና የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር በጉምሩክ አገልግሎቶች ዙሪያ በትብብር በሚሰሩባቸው የዕቅድ ሥራዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል።
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አዝዘው ጫኔ፤ በሕግና የአሰራር ሥርዓት የተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች የጉምሩክ አገልግሎቱን እያሳለጡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሕግና የአሰራር ሥርዓት ማሻሻያውን ተከትሎም የመድኃኒት አምራችና የሕክምና መሳሪያ አምራቾችን የጉምሩክ አገልግሎት ስትራቴጂክ አጋርነት ማጠናከር እንዳስቻለ አንስተዋል።
በዚህም ለሀገር ውስጥ የመድኃኒትና የሕክምና መሳሪያ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ምቹ የጉምሩክ አገልግሎት ምኅዳር በመፍጠር ምርታማነታቸውን እያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድኃኒትና የሕክምና መሳሪያ አምራቾች፣ ላኪና አስመጪዎች የሚቀርቡ አገልግሎቶችን በማሳለጥ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።
በቀጣይም በትብብር የሚሰራባቸውን የጋራ ዕቅዶችን በባለድርሻ አካላት በማዳበር ውጤት በሚያስገኝ አግባብ ተግባራዊ እንደሚሆኑ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሰ ተፈሪ፤ የፋርማሲቲካል ዘርፍ የጉምሩክ አገልግሎቶች ማሻሻያ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል።
የኮሚሽኑ የሕግና የአሰራር ማሻሻያም ለመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያ አምራቾች የጉምሩክ አገልግሎት መሳለጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የዘርፉን ምርታማነት በማሳደግና አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በመፍጠር በዜጎች የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ላይ ትልቅ አቅም እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
የሀገር ውስጥ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያ አምራቾችም ከውጭ የሚያስገቧቸውን ጥሬ ዕቃዎች በፍጥነት የሚያስገቡበት ምቹ ምኅዳር መፍጠር እንዳስቻለም አንስተዋል።