ቀጥታ፡

ኮሌጆች ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ለማሳካት  የማይተካ ድርሻ አላቸው

ቦንጋ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ለማሳካት በሚደረገው ርብርብ ብቃት ያለው የሰው ሀይል በማፍራት የማይተካ ድርሻ እንዳላቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ኢትዮ ኮደርስ ስልጠናና ፋይዳ መታወቂያን ተደራሽ ለማድረግ ያለመ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።


 

በመድረኩ የተገኙት የቢሮ ምክትል ሀላፊና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ምትኩ አስፋው እንደገለጹት፤ ኮሌጆች ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ለማሳካት በሚደረገው ርብርብ ብቃት ያለው የሰው ሀይል በማፍራት የማይተካ ሚና አላቸው፡፡

ለዚህም ራሳቸውን በቴክኖሎጂ ግብአቶች በማደራጀት ለሰው ሀይል ልማት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አክለዋል።

ለዲጂታል ኢትዮጵያ መሳካት ድርሻ ላላቸው የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እና ለፋይዳ መታወቂያ ኢንሼቲቮች ትኩረት መስጠት ሌላው ተግባራቸው መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በክልሉ በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በዓመት ከ110 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እስካሁን ድረስ 28 ሺህ 90 ሰዎች እንደወሰዱና 8 ሺህ የሚጠጉትም ሰርተፊኬት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ዜጎችን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር በዓመቱ ለማሳካት ከታቀደው ውስጥ እስካሁን ድረስ 246 ሺህ 436 ዜጎችን የመታወቂያው ባለቤት ለማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።

ሥራውን ለማሳካትም የአሁኑ የንቅናቄ መድረክ ተደማሪ አቅም ይሆናል ብለዋል።


 

በመድረኩ የተገኙት የካፋ ዞን ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን መምሪያ ሀላፊ አቶ ተፈሪ ታደሰ በበኩላቸው፤ በዞኑ በኮደርስ ስልጠና  በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሥራዎች እንደተጀመሩና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ኢንሼቲቮቹን ለማሳካት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሁለተኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ መደረጉንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም