በነቀምቴ ከተማ የህብረተሰቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በነቀምቴ ከተማ የህብረተሰቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው
ነቀምቴ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦ በነቀምቴ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የህብረተሰቡን ኑሮ እያሻሻሉ መሆኑን መመልከታቸውን በከተማዋ ጉብኝት ያደረጉ የተለያዩ ክልሎች የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊዎች ገለጹ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም በነቀምቴ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
በግምገማ መድረኩ የተገኙ የተለያዩ ክልሎች የውሃ እና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊዎች በነቀምቴ ከተማ እና አካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማዕድን እና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን መኔዶ፣ የኮሪደር ልማት ስራ ከተሞችን እያነቃቃ መሆኑን ተናግረዋል።
በነቀምቴ ከተማም ኮሪደርን ጨምሮ እየተከናወኑ ያሉ አጠቃላይ የልማት ስራዎች ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ማድረግ ማስቻሉን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ስራው ለከተማዋ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ያስቻለ መሆኑን ጠቅሰው ለሌሎች ከተሞችም ተሞክሮ የሚሆን መሆኑን አስረድተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የውሃ፣ ኢነርጂ እና መስኖ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ፣ በአካባቢው የሰፈነው ሰላም የልማት እንቅስቃሴ እንዲፋጠን ማስቻሉን መገንዘባቸውን ጠቁመዋል።
በሌሎች ከተሞች የተጀመሩ የኮሪደር ስራዎች እና ከተማን የማዘመን ስራ በነቀምቴ ከተማም በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ማየታቸውን አመልክተዋል።
በነቀምቴ ከተማ የተመለከቱት የልማት እንቅስቃሴ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሀረሪ ክልል የውሃ እና ፍሳሽ ቢሮ ሀላፊ ተወካይ አቶ ኤርምያስ ተካልኝ ናቸው።
በተለይም የኮሪደር ልማት ስራ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ እና ማጣሪያ ግንባታ እና የንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለከተማዋ ትልቅ ጠቀሜታ የሚሰጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በተለይ የፍሳሽ ማስወገጃ እና ማጣሪያው በሀገሪቱ ጥቂት ከተሞች ብቻ የተጀመረ መሆኑን አንስተው ስራው ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን አመልክተዋል።
የጉብኝቱ ተሳታፊዎች መንግስት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን በሁሉም አካባቢዎች እየተገበረ መሆኑን መረዳታቸውን አንስተዋል።