በአስተዳደሩ በበጋ መስኖ ልማት 4 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በአስተዳደሩ በበጋ መስኖ ልማት 4 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል ተሸፍኗል
ደብረ ብርሃን፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦ በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በበጋ መስኖ ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል እየለማ መሆኑን የአስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ መርሻ ዓይሳነው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጨማሪ ምርት በማግኘት ከተረጂነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው።
በዚህም በተያዘው የበጋ ወራት በከተማ አስተዳደሩ 4 ሺህ 185 ሄክታር መሬት በስንዴ እየለማ መሆኑን ገልጸው፣ ከዚህም ከ64 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱን ምርታማነት ለማሳደግም የዘመናዊ ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘርና ሌሎች የምርት ማሳደጊያ ግብአቶች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም 101 የውሃ መሳቢያ ጀነሬተሮችን ለአርሶ አደሮች በማሰራጨትና በትራክተር ጭምር በመታገዝ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።
በመስኖ ልማት ሥራው ከተሰማሩ አርሶ አደሮች መካከል ደምሴ አሰፋ እንዳሉት፤ባለፈው ዓመት በግማሽ ሄክታር መሬታቸው ላይ ስንዴ በመስኖ በማልማት ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ከ250ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ዘንድሮም ካለፈው ዓመት ተሞክሮ ወስደው ሥራቸውን በማስፋፋት በአራት ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ ስንዴ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሌላው የመስኖ ልማት ተሳታፊ ቄስ መንገሻ ተክለወልድ በበኩላቸው፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከመጣ ወዲህ የዝናብ ወቅትን ሳይጠብቁ በማምረት የምግብ ሉአላዊነታቸውን እያረጋገጡ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ከተጀመረ ወዲህ የስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ የአገር ውስጥ ፍጆታን ከመሸፈን ባለፈ ለውጭ ገበያ መላክ መጀመሩ የሚታወስ ነው።