ቀጥታ፡

የጤና መድህን ሽፋንን ማሳደግ  የጤና አገልግሎትን በፍትሃዊነት ለማዳረስ ወሳኝ ሚና ይጫወታል 

ድሬዳዋ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦ የጤና መድህን ሽፋንን ማሳደግ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎትን ለማዳረስ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ።

የ2018 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የአባላት ምዝገባና ዕድሳት ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በድሬዳዋ ተጀምሯል።


 

በንቅናቄ መድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ጤና መድን አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ያምሮት አንዱአለም፣ በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጤና መድህን ሽፋንን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ባለፈው ዓመት ብቻ ከ63 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

የጤና መድህን አገልግሎት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

ከፍለው መታከም የማይችሉ 17 ሚሊዮን ዜጎችም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለዚህም  መንግስት ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጎማ ማድረጉን አመልክተዋል።

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እስካሁን 73 በመቶ ነዋሪዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፣ በቀጣይም ይህን የማላቅ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የድሬዳዋ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የቦርድ ሰብሳቢ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው፤ በከተማዋ የጤና መድህን አገልግሎት ሽፋንን ወደ 95 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋትና ማህበራዊ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ቢሮ ኃላፊ ፅጌረዳ ክፍሌ (ዶ/ር) ናቸው።

በንቅናቄው መድረክ ላይ የተሳተፉት የገጠርና የከተማ የጤና ዘርፍ አመራሮች በዘርፉ የተገኙ አበረታች ውጤቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት  እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም