የአፍሪካ ህክምና ግብዓት አምራቾች አውደ ርዕይና ጉባኤ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን አቅም ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህክምና ግብዓት አምራቾች አውደ ርዕይና ጉባኤ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን አቅም ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህክምና ግብዓት አምራቾች አውደ ርዕይና ጉባኤ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን አቅም ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና እንዳለው የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ ገለጹ።
"ሶስተኛው የአፍሪካ ህክምና ግብዓቶች የንግድ፣ አውደ ርዕይና ጉባኤ 2026" ከመስከረም 25 እስከ 27 ቀን 2019 በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ አውደ ርዕይና ጉባኤውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያስመዘገበችው ስኬትና የግሉን ዘርፍ ለማበረታታት የሰጠችው ትኩረት አውደ ርዕይና ጉባኤውን እንድታዘጋጅ አስመርጧታል።
በዝግጅቱ ላይ የህክምና ግብዓት አምራቾች፣ የፋይናንስ አቅራቢዎች፣ የፈጠራ ባለቤቶች፣ ኢንቨስሮች፣ ተመራማሪዎች እና ከ600 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በዘርፉ ለተሰማሩ አምራቾች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚከናወኑ ተግባራት መጠናከራቸውንም ገልጸዋል።
ከመሰረት ልማት አቅርቦት አኳያ የህክምና ግብዓቶች የሚመረቱባቸው ልዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዝግጁ መሆናቸውንም እንዲሁ።
ከዚህ አኳያም ሶስተኛው የህክምና ግብዓት አምራቾች አውደ ርዕይና ጉባኤ ኢትዮጵያ በዘርፉ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት እና አቅሞችን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የህክምና ግብዓት አምራቾች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሰ ተፈሪ በበኩላቸው፤ አውደ ርዕይና ጉባኤው ለሀገር ውስጥ አምራቾች የገበያ ትስስር ለመፍጠር ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የአፍሪካ ህክምና ግብዓት አምራቾች የንግድ፣ አውደ ርዕይና ጉባኤ ሴክሬታሪያት ሊቀ መንበር እንማሬ ሆሳንግ በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚችሉ መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።
አውደ ርዕይና ጉባኤው መሰል ስራዎች እንዲጠናከሩ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም ባሻገር በአፍሪካ ያሉ ባለድርሻ አካላትን በማገናኘት ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።