በኦሮሚያ ክልል የአርብቶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል በተሰራው ስራ ውጤት እየተገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የአርብቶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል በተሰራው ስራ ውጤት እየተገኘ ነው
አዲስ አባባ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ድርቅን መቋቋም የሚያስችል አቅምን በማጎልበት የአርብቶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል በተሰራው ስራ የተሻለ ውጤት እየተገኘ መሆኑን የክልሉ መስኖ ልማትና አርብቶ አደር ቢሮ ገለጸ።
የኦሮሚያ ክልል የመስኖና አርብቶ አደር ቢሮ ምክትል ሀላፊ ኢንጂነር አለሙ ረጋሳ እንደተናገሩት፤ የአርብቶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል የውሃ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።
አርብቶ አደሩ ከእንስሳት እርባታው ጎን ለጎን በግብርና ስራ ላይ በመሳተፍ የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ እንዲችል 'ፊና ኦሮሚያ' የተሰኘ ፕሮጀክት ተቀርጾ ሲተገበር ቆይቷል ብለዋል።
በ2014 ዓ.ም ከተጀመሩ 73 የፊና ፕሮጀክቶች ውስጥ 37ቱ ግንባታቸው ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን የተቀሩት ፕሮጀክቶች ደግሞ በግንባታ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በፕሮጀክቱ አነስተኛ እና መካከለኛ የመስኖ ግድቦች በብዛት የተገነቡ ሲሆን አርብቶ አደሩ ግድቦቹን ለእንስሳት መጠጥ ውኃ እና ለግብርና ልማት እየተጠቀመበት መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም አነስተኛ ግድቦቹ ለእንስሳት መኖ ልማትም እየዋሉ በመሆኑ አርብቶ አደሩ ከእንስሳት ሀብት ልማቱ ተጠቃሚ መሆን መጀመሩን ተናግረዋል።
ይህ ብቻ ሳይሆን አርብቶ አደሩ በተለያየ ምክንያት በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ወደ ኋላ የቀረ መሆኑን አስታውሰው መሰረተ ልማትን የማሟላት ስራም በስፋት መከናወኑን ገልጸዋል።
ከመሰረተ ልማቶቹ መካከል መንገድ፣ መብራት፤ የጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ማስፋፋት ስራ መሰራቱን ጠቅሰው በዚህም አርብቶ አደሩ ድርቅ የመቋቋም አቅሙን በማሳደግ ምርታማ እንዲሆን እየተደረገ ነው ብለዋል።
በቀጣይም አርብቶ አደሩ ድርቅን የመቋቋም አቅሙን በማጎልበት ህይወቱን ለማሻሻል የተጀመረው ስራ እንደሚጠናከርም ገልጸዋል።
በቢሮው የኮንትራክተር አስተዳደር ዳይሬክተር ኢንጂነር ተመስገን ሩንዳሳ በበኩላቸው፤ በክልሉ በከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውሃ በአግባቡ በመጠቀም የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በግንባታ ላይ የሚገኙ የመስኖ ግድቦችን ፈጥኖ ለማጠናቀቅም የተጀመረው ስራ ይጠናከራል ብለዋል።