ቀጥታ፡

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ አጋዥ ሚና ይኖረዋል   

አክሱም ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ትግበራ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ አጋዥ ሚና እንደሚኖረው የአክሱም ከተማ መምህራን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ቀጣይ 5 ዓመታት የዲጂታል ጉዞ የሚመራበትን ''ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ'' በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው  ይታወሳል።

ዲጂታል ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ የመፈጸም አቅም በማሳደግና የሀገርን ልማት በማሳለጥ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ሥብራትን ለመጠገን እየተደረገ ያለውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ የቴክኖሎጂ ተደረሽነትን ማስፋት ቁልፍ ጉዳይ ነው።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአክሱም ከተማ መምህራንም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ።


 

በአክሱም የአልሙናይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ያሬድ መኮንን፣ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ተማሪዎችን በቂ ዕውቀት ለማስጨበጥ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

የፈተና አሰጣጡ በዲጂታል ቴክኖሎጂ መታገዙም ኩረጃን የሚያስቀርና የፈተና ደህንነትን የሚያስጠብቅ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ትግበራ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ አጋዥ ሚና እንደሚኖረው በመግለጽ።

መምህር ሙዑዝ በየነ በበኩላቸው፣ የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ትግበራ ተማሪዎች ተግባር ተኮር ዕውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ ያግዛል ብለዋል።


 

የመማር ማስተማር ሂደቱን ፈጣንና ቀልጣፋ ከማድረግ ባለፈ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ስትራቴጂው ተማሪዎች አጋዥ መጽሐፍትን በቀላሉ እንዲያገኙና የዕውቀት አድማሳቸውን እንዲያሰፉ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ያሉት ደግሞ መምህር ግደይ ካሓሱ ናቸው።


 

በትምህርት ጥራት ላይ ይነሳ የነበረውን ተደጋጋሚ ቅሬታ ለመፍታትም ከፈተና አወጣጥ ጀምሮ ያለውን ሂደት ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን ያግዛል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም