በዞኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
ነገሌ ቦረና ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን በሁሉም ዘርፍ በመከናወን ላይ ያሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የዞኑ ገንዘብ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በጽህፈት ቤቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቡድን መሪ አቶ አንድነት አበበ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰው ተኮር ልማቶች በመከናወን ላይ ናቸው።
ለዚህም ተፈጻሚነት አብይ እና የቴክኒክ ኮሚቴ በየደረጃው በማዋቀር በልዩ ትኩረት እየተመራ መሆኑን ገልጸው በአገልግሎቱም በዘጠኝ ወረዳዎች የተውጣጡ ከ200 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በዚህ ተግባር ካለፈው ክረምት ወዲህ የአረጋዊያን ቤት እድሳትና ግንባታ፣ በከተሞች ጽዳትና ውበት፣ የመጠጥ ውሃ፣ የትምህርት እና የመንገድ መሠረት ልማት፣ ደም ልገሳ፣ አረንጓዴ አሻራ እንዲሁም ሌሎችም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በተለይ እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ 877 አዲስ መኖሪያ ቤት ግንባታ እና ከ1 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች እድሳት በማድረግ አቅመ ደካሞችንና አረጋዊያንን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚተዳደሩ ለ15 ሺህ 625 ቤተሰቦች 18 ሚሊዮን ብር የጤና መድህን ዋስትና ኢንሹራንስ በበጎ ፈቃደኞች መሸፈኑንም ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ለበርካታ ሰዎች ነፃ የስኳር፣ የደም ግፊት እና የማህጸን ጫፍ ካንሰር ምርመራ እንዲሁም ነፃ የአይን ሞራ ግርዶሽ ምርመራ እና ህክምና መሰጠቱን አብራርተዋል።
ወጣቶች እና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች በበጎ ፈቃድ ስራዎች በመሳተፍ የገንዘብ፣ የጉልበት እና የዕውቀት ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን በዚህም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል።
አሁን ላይም የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን ለማጠናከር እየተሰራ ሲሆን በተለይ በበጋ ወራት የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃና እንክብካቤ መጀመሩን ገልጸዋል።
በተለይ የአካባቢ መራቆትን በዘላቂነት ለመቋቋም እንዲቻል 32 ሚሊዮን ችግኞች የማፍላት ስራ እየተካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል።