ቀጥታ፡

ጥራት ያለው የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦ ጥራት ያለው የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን ለማጠናከርና ፍትሐዊ የሕክምና ሥርዓትን ለማስፈን ትኩረት መሰጠቱን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ገለጸ።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጤና መድህን ሥርዓት ዜጎች በሕክምና ወቅት የሚያጋጥማቸውን የክፍያ ስጋት በማስቀረት፣ አካታችና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል ነው፡፡

በዚህም አሁን ላይ በመላ ሀገሪቱ 13 ነጥብ 67 ሚሊዮን አባወራና እማወራዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከ63 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የጤና መድህን ተጠቃሚ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በርካቶች የአገልግሎቱን አስፈላጊነት በመረዳት ተጠቃሚ መሆናቸው በጤናው ዘርፍ የእርስ በርስ መደጋገፍና የመረዳዳት ባሕል እንዲጎለብት አድርጓል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በ1 ሺህ 195 ወረዳዎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በ2018 ዓ.ም እየተከናወነ በሚገኘው አዲስ ምዝገባም ተጨማሪ 72 ወረዳዎችን ወደ ሥርዓቱ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ቀልጣፋና ግልጽ ለማድረግም የፋይዳ (ብሔራዊ) መታወቂያ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


 

በጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምና ሲከታተሉ ያገኘናቸው አቶ ከማል ሀሰን እና ሱልጣን አብደላ የጤና መድህን ተጠቃሚ በመሆናቸው የቀዶ ሕክምናና የመድኃኒት አገልግሎትን በተፋጠነ መንገድ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሥርዓቱ አቅም የሌላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎችን እየታደገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ሽቱ አበራ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል ለሕክምና አገልግሎት ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቅ ተገቢውን ሕክምና ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።

አሁን ግን በዓመት አንድ ጊዜ በሚከፈል አነስተኛ መዋጮ ከቀላል ሕመም እስከ ከፍተኛ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።

እስካሁን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ያልሆኑ ዜጎች መንግስት ያመቻቸውን ወሳኝ የሕክምና ዋስትና እንዲጠቀሙ መክረዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም