ቀጥታ፡

የኃይማኖት ተቋማት ለሰላም እሴት ግንባታና ለህዝብ አብሮነት ያላቸውን ሚና የበለጠ ያጠናክራሉ

አሶሳ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦ የኃይማኖት ተቋማት በኢትዮጵያ የሰላም እሴት ግንባታና ለህዝቦች አብሮነት ያላቸውን ሚና የበለጠ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀኃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ በሰላም እሴት ግንባታ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሃፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የኃይማኖት ተቋማት ካለባቸው ኃላፊነት መካከል የህዝብ አንድነትና አብሮነትን ማጠናከርና የሰላም እሴቶችን ማጎልበት ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል።

የኃይማኖት ተቋማቱ ዋና አስተምህሮም ሰላምና ፍቅርን መስበክ፣ መረዳዳትና መተጋገዝን ማጠናከር መሆኑን አንስተዋል። 

የህዝቦች ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከርና አለመግባባቶችን በውይይትና በንግግር መፍታትም የኃይማኖት ተቋማቱ ዋነኛ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

የቤንሻንኩል ጉሙዝ ክልል ያለው የኃይማኖት ብዝሃነት በሰላም ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸው፣ በክልሉ የሰፈነውን ሰላም ለማጽናት ተቋማቱ ሚናቸውን የበለጠ ያጠናክራሉ ብለዋል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሠላም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ ቢኒያም መንገሻ በበኩላቸው፣ በክልሉ ለተገኘው ሰላም የኃይማኖት ተቋማቱ የማይተካ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።

ቀጣይም የክልሉ መንግስትና የጸጥታ አካላት ከኃይማኖት ተቋማት ጋር ጠንካራ ቅንጅት በመፍጠር የሰላም እሴት ግንባታውን የበለጠ ውጤታማ የሚያደርጉ ሥራዎችን እንሰራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም