በመጪው ምርጫ በሐሳብ የበላይነት ለመፎካከር ተዘጋጅተናል-የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
በመጪው ምርጫ በሐሳብ የበላይነት ለመፎካከር ተዘጋጅተናል-የፖለቲካ ፓርቲዎች
ወላይታ ሶዶ፣ጥር 15/2018 (ኢዜአ):- በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ በሐሳብ የበላይነት ለመፎካከር ተዘጋጅተናል ሲሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ ይታወቃል።
በወጣው መርሃ ግብር መሰረት ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው።
በመሆኑም በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚሳተፉት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው በሐሳብ የበላይነት ለመፎካከር ተዘጋጅተናል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ እና የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ምክትል ሊቀመንበር ጎበዜ አበራ፤ በጋራ ምክር ቤቱ የሚገኙ ሁሉም ፓርቲዎች ለምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ የበኩላቸውን ለመወጣት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በምርጫው ሂደት ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ አሰራር በመከተል የምርጫ ምልክቶቻቸውን ለቦርዱ የማሳወቅ፣ ዕጩዎችን የማስመዝገብና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለማከናወን መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።
ምርጫው ሰላማዊ፣ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ነፃ እንዲሆን ምክር ቤቱም ሆነ ፓርቲያቸው የበኩሉን አስተዋጾ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።
በምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባና ሌሎች ተግባራትን በኦንላይን ለማከናወን የሚያስችል ዝግጁነት መኖሩ ደግሞ የፓርቲዎችን ድካም የሚያቃልል እንዲሁም ለፈጣንና ግልጽ አሰራር አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ተናግረዋል።
የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ማቱሳል ማላቆ፤ የፓርቲውን ፖሊሲ በመከለስና የምርጫ ስትራቴጂ በማዘጋጀት ለሰላማዊ ፉክክሩ ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ መሆኑን ገልጸዋል።
የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ መምጣት ሁሉም ፓርቲዎች የሚወዳደሩበትን ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸው፣ ይህን ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የህዝብን ድምጽ ለማግኘት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በምርጫው የተሻለ ሀሳባ ይዞ በመቅረብ ለመፎካከር እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸው፣ በእስካሁኑ ሂደት ፓርቲው ለሚያቀርባቸው እጩዎች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል።
የወላይታ ህዝብ ዴሞክራሴያዊ ግንባር (ወህዴግ) ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምልኪያስ ሳንታ በበኩላቸው፥ ፓርቲያቸው ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ ባሉ ሂደቶች ፓርቲው በንቃት በመሳተፍ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጸው፥ በምርጫው የተሻለ ሀሳብ በማንጸባረቅ ለመፎካከር መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።