ባዮ ጋዝ በመጠቀማችን ጤንነታችንን መጠበቅ ችለናል- አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ባዮ ጋዝ በመጠቀማችን ጤንነታችንን መጠበቅ ችለናል- አርሶ አደሮች
ጎንደር ፤ ጥር 15/2018 (ኢዜአ)፡- ባዮ ጋዝ መጠቀም በመቻላቸው ከሚያገኙት ጥቅም በሻገር ጤንነታቸውን ለመጠበቅ እንዳገዛቸው የማእከላዊ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ፡
በዞኑ ዘንድሮው ዓመት 180 የባዮ ጋዝ ማብላያዎች የግንባታ ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተመልክቷል።
በማእከላዊ ጎንደር ዞን የምእራብ በለሳ ወረዳ ነዋሪ አቶ መኳንንት የአብስራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤የባዮ ጋዝ ማብላያ በመገንባት ላለፉት ሶስት ዓመታት ለምግብ ማብሰልና ለመብራት እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
ይህም ቀደም ሲል ለምግብ ማብሰያና ለመብራት አገልግሎት ማገዶን በመጠቀም ጭሱ በጤናቸው ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስና ለሀይል አቅርቦት ይጨፈጭፍ የነበረን ደን ለመጠበቅ እንደቻሉ ገልጸዋል።
የባዮ ጋዙ ለኃይል አቅርቦት ከመዋሉም ባሻገር ተረፈ ምርቱን ለመሬታቸው የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም ምርታማነታቸውን ማሳደግ መቻላቸውን የገለጹት ደግሞ የወገራ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር በላይ ቸርነት ናቸው፡፡
የባዮ ጋዝ ሃይል አቅርቦቱ ለአጠቃቀም ቀላልና ልጆቻቸው ትምህርታቸውን በማታ ለማጥናት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።፡
በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የምንዝሮ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ተሾመ ንጉሴ በበኩላቸው የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ሴቶችና ህጻናትን ማገዶ ፍለጋ ይደርስባቸውን የነበረውን መንከራተት ያስቀረ ነው ብለዋል፡፡
በማእከላዊ ጎንደር ውሃና ኢነርጂ መምሪያ የፕላንና ፕሮግራም ቡድን መሪ አቶ ማሩ ታደሰ እንደገለጹት፤ በዘንድሮ ዓመት በ13 ወረዳዎች 180 የባዮ ጋዝ ማብለያዎች ግንባታ ለማከናወን እየተሰራ ነው።
እስካሁንም ተጠቃሚ አርሶ አደሮችን መለየት፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን የማቅረብና አርሶ አደሩ እንደ አሸዋና ድንጋይ ያሉ የአካባቢ ቁሳቁሶችን እንዲያቀርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የባዮ ጋዝ ማብለያዎቹን ግንባታ በዚህ ዓመት መጨረሻ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት በማብቃት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።