በክልሉ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ጀምሮ የመጨረስ ባህል እያደገ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ጀምሮ የመጨረስ ባህል እያደገ መጥቷል
ወላይታ ሶዶ/አርባ ምንጫ/ዲላ፤ ጥር 15/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ለፕሮጀክቶች አፈጻጸም በተሰጠ ትኩረት ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ጀምሮ የመጨረስ ባህል እያደገ መጥቷል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
ለክልሉ መንግስት የተለያዩ አገልግሎት መስጫ የሚውሉ ሕንጻዎች ግንባታ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
በክልሉ ወላይታ ሶዶ ከተማ ለሚገነባው የርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት እና የቤተ መንግስት ሕንፃ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ናቸው።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህን ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ለማይሰሩ ፕሮጀክቶች መሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ታሪክ ተቀይሮ አሁን ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ጀምሮ የመጨረስ ባህል እያደገ መጥቷል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ስድስት ማዕከሎች የሕንጻ ግንባታ ሥራ መጀመሩን ገልጸው፤ ዘመናዊ ሕንጻዎቹ የህዝቡን ባህል፣ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠትና የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተገነቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ግንባታዎቹን የሚያካሂዱት ሥራ ተቋራጮች ሥራውን በተያዘለት የጊዜ ገደብ በማጠናቀቅ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበው፣ የክልሉ መንግስትና ህዝብ ለስራው መሳለጥ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋሉ ብለዋል።
በተመሳሳይ ዜና በአርባ ምንጭ ማዕከል ለሚገነባው ሕንጻ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) የመሰረት ድንጋይ አስቀምጥዋል።
በዚህ ወቅት አበባየሁ (ዶ/ር) እንዳሉት በክልሉ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎትና የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በክልሉ ፍትሃዊ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ህዝብን ያሳተፈ ሥራ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የክልል ቢሮዎች ግንባታቸው ሲጠናቀቅ ለከተማው ተጨማሪ ውበት ከመሆን ባለፈ ህብረተሰቡ የተለያዩ አገልግሎቶችን በቅርበት እና በአንድ ማዕከል እንዲያገኝ ስለሚያስችሉ ወጪና እንግልቱን ያስቀርለታል ብለዋል።
በዲላ ከተማ ለሚገነባው የቢሮ ሕንጻ የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት በተለያዩ ከተሞች ግንባታቸው የተጀመረው የቢሮ ሕንጻዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና ጥራት እንዲጠናቀቁ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል።
በከተማው ዛሬ የመሰረት ድንጋይ የተጣለለት ሕንጻ ሲጠናቀቅ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት በተሻለ በማድረግ ህዝቡን ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
በተለያዩ ከተሞች ለሚገነቡና በግንባታ ሂደት ላይ ላሉ የቢሮ ሕንጻ ፕርጀክቶች 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መመደቡን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ድርጅት ምክትል እና የምህንድስና ዘርፍ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ ነጋ ናቸው።