የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራውን በትጋት በመወጣት ለሀገራዊ እድገት የሚኖውን ፋይዳ ለማሳካት በትኩረት እንሰራለን - ኢዜአ አማርኛ
የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራውን በትጋት በመወጣት ለሀገራዊ እድገት የሚኖውን ፋይዳ ለማሳካት በትኩረት እንሰራለን
አምቦ፤ጥር 15/2018(ኢዜአ)፡- የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራውን በትጋት በመወጣት ለሀገራዊ እድገት የሚኖውን ፋይዳ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰሩ ሰልጣኞች ገለጹ።
በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የአምቦ ቅርንጫፍ በ2ኛው ዙር የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ላይ ለሚሰማሩ መረጃ ሰበሳቢዎች እና ተቆጣጣሪዎች ስልጠና ሰጥቷል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ሰልጣኞች ጥራት ያለውን የኢኮኖሚ ድርጅቶች መረጃ በአግባቡ በመሰብስብ ለሀገር እድገት ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ ከሰልጣኞች መካከል ኪቢቱ ጋረደው፣ ስልጠናው ጥራት ያለውን መረጃ ከህብረተሰቡ ለመሰብሰብ እንደሚያግዛት ገልጻለች።
ይሄም መንግስት የህብረተሰቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ለሚያደርገው ጥረት መሰረት እንደሚሆንም ገልጻለች።
ሌላው ሰልጣኝ አቶ ፀጋዬ ጌታቸው እንዳሉት፤ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ መረጃዎቹን በትክክል ለመሰብሰብ ዲጂታል ቴክኖሎጅን እንደሚጠቀም ገልጿል።
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የጥናት፣ ምርምርና ስልጠና ክፍል መሪ ስራ አስፈፃሚ ሶርሴ ጉተማ እንዳሉት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ 2ኛ ዙር የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በ55 የስልጠና ማዕከሎች እየተሰጠ ነው።
ቆጠራውን በተደራጀ መልኩ ለመምራት የመንግስት የልማት ድርጅት፣ የግል ኢኮኖሚ ድርጅቶች፤ ባለሃብቶች እና ሌሎች አካላት ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራው የኢኮኖሚ ዘርፉን ሁኔታና የሀገሪቷን ጠቅላላ ሀብት ለማወቅና የፖሊሲ አማራጮችን ለማውጣት እንዲሁም ምርምሮችን ለማካሄድ ማለሙን ተናግረዋል ፡፡
በአገልግሎቱ የአምቦ ስታቲክስ አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽህፈትቤት ኃላፊ አቶ አቡና ገደፋ በበኩላቸው፤ እየተሰጠ ያለው ስልጠና መረጃ ሰብሳቢዎች ጥራትና ወቅቱን የጠበቀ መረጃን መሰብሰብ የሚችሉበትን አቅም ለመገንባት ነው ብለዋል።
ለዚህም 3 ሺህ 145 መረጃ ሰብሳቢ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠናውን በመውሰድ በአካባቢው ያሉ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ላይ ይሰማራሉ ነው ያሉት።