የኢትዮጵያን የስፖርት ቱሪዝም ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የስፖርት ቱሪዝም ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የስፖርት ቱሪዝም ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።
የስፖርት ቱሪዝም በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣ የቱሪዝም ዘርፍ ነው።
በኢትዮጵያም በአትሌቲክስ፣ በጎዳና ላይ ሩጫ፣ ባሕላዊ እና ሌሎች የጉብኝት ቦታዎች የእግር ጉዞ የስፖርት አይነቶች ለስፖርት ቱሪዝም ተጠቃሚነት ምቹ አቅሞች ናቸው።
የኢትዮጵያ የስፖርት ቱሪዝም አቅሞችም በሀገር ገጽታ ግንባታ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በማሳደግና በስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው።
የአዲስ አበባና ሌሎች ዋና ዋና ከተሞች የኮሪደር ልማትም በስፖርት ማዘውተሪያ ስታዲየም ግንባታ፣ በብስክሌትና በእግር መንገድ የስፖርት ዘርፎች ለስፖርት ቱሪዝም ዕድገት ወሳኝ ምዕራፍ ከፍተዋል።
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በጥቂት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ለስፖርት ቱሪዝም እንቅስቃሴ ምቹ ምኅዳር መፍጠር አስችለዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ መኪዩ መሐመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አዲስ አበባን ለስፖርት ቱሪዝም ምቹ ለማድረግ የተሰሩ ተግባራት ከፍተኛ ውጤት እያስገኙ ነው ብለዋል።
በተለይም የመዲናዋ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከልነት እያደገ መምጣት ለስፖርት ቱሪዝም እንቅስቃሴ ወሳኝ ምዕራፍ መክፈቱን ገልጸዋል።
በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት 16 ዓለም አቀፋዊ የስፖርት ሁነቶችን በስኬት በማስተናገድ ኢትዮጵያ ለስፖርት ቱሪዝም አቅም እንዳላት በተግባር ማሳየት እንደተቻለ ተናግረዋል።
ለአብነትም በየዓመቱ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች የሚሳተፉበት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እና 46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በስኬት መስተናገዳቸውን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በስፖርት ቱሪዝም የሚስተናገዱ ሁነቶችም በሀገር ገጽታ ግንባታና በውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲሁም የስፖርት መሠረተ ልማትን በማስፋፋት አዎንታዊ ሚና እንዳላቸው አብራርተዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያ 32 ብሔራዊ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ዓለም አቀፍ የስፖርት ሁነቶችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያመጡ በትብብር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የሚካሄዱትን 5ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክና የአፍሪካ የባህል ስፖርት ፌስቲቫል ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያን የስፖርት ዲፕሎማሲ እና ስፖርታዊ ኩነቶች የማስተናገድ አቅም በማሳደግ ቀዳሚ የአፍሪካ የስፖርት ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።