ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ አላማ ያደረገው የሐዋሳ ሀይቅ ግማሽ ማራቶን የካቲት 1 ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ አላማ ያደረገው የሐዋሳ ሀይቅ ግማሽ ማራቶን የካቲት 1 ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2018 (ኢዜአ)፦ 14ኛው የሐዋሳ ሀይቅ ግማሽ ማራቶን የካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስታወቀ።
ውድድሩ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ኢትዮ ቴለኮም እና ሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር የሚያዘጋጀው ነው።
በዘንድሮው ውድድር ከአዲስ አበባ እና ከውጭ ሀገራት ወደ ሐዋሳ የሚመጡ ከ500 በላይ ተሳታፊዎች የሚጠበቁ ሲሆን የሐዋሳ ከተማ እና አካባቢዋ ነዋሪዎችን ጨምሮ ወደ አምስት ሺህ የሚጠጉ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት ውድድር እንደሚሆን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለኢዜአ በላከው መግለጫው አመልክቷል።
በተጨማሪም በውድድሩ ላይ ከ21 በላይ ሀገራት እና ከሁሉም አህጉራት የተውጣጡ ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉ ያመለከተው መግለጫው ይህ ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎ ሐዋሳ ያላትን ትልቅ የቱሪስት መዳረሻነት ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጿል።
14ኛው የሐዋሳ ሀይቅ ግማሽ ማራቶን በስድስት የክልል ከተሞች የሚካሄደው የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ (Discover Ethiopia Classics) ተከታታይ ውድድሮች አካል ነው።
ይህ በደብረ ብርሃን ከተማ የተጀመረው የስድስት ከተሞች ውድድር የሀገሪቱን ተፈጥሮ እና ባህል ለሌሎች ለማስተዋወቅ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተጠቁሟል።
ሐዋሳ የዚህ ውድድር ሁለተኛ መዳረሻ ከተማ ስትሆን ጅማ ፣ በቆጂ፣ አርባ ምንጭ እና ሐረር በቀጣዮቹ ወራት ተመሳሳይ የውድድር እና የጉብኝት ቀናት እንደሚኖራቸው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያስታወቀው።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ ስለ የሐዋሳ ሐይቅ ግማሽ ማራቶን ከሩጫው ባለፈ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ውበት እና እንግዳ ተቀባይነት የምናከብርበት ዝግጅት ነው ብለዋል።
ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሐዋሳን የስፖርት እና የቱሪስት መዳረሻ ማዕከልነቷን ለማሳደግ በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ሐዋሳ ዓለም አቀፍ አትሌቲክስን ለሚፈልጉ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ሊጎበኟት የሚገባ መዳረሻ መሆኗ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ውድድሮች መታዩትን አውስተዋል።
ዝግጅቱ ከዋናው የ21 ኪሎ ሜትር ውድድር በተጨማሪ የ8 ኪሎ ሜትር የህዝብ ሩጫ እና የህፃናት ሩጫዎችን የሚያካትት ነው።
ከሩጫውም ባለፈ በታቦር ተራራ ላይ የሚደረግ የእግር ጉዞ እና ልዩ የቱሪስት መስህቦችን ጉብኝት እንደሚደረግ ተገልጿል።
በስድስት የክልል ከተሞች የሚካሄደው የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ (Discover Ethiopia Classics) ጥር 3 ቀን 2018 ዓ.ም በደብረ ብርሃን በተካሄደ ውድድር መጀመሩ የሚታወስ ነው።