ቀጥታ፡

በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን ጨምሮ ከ400ሺህ በላይ መጽሐፍት በዲጂታል ሥርዓት ተደራጅተዋል

ጎንደር፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎችን ጨምሮ ከ400ሺህ በላይ መጽሐፍት በዲጂታል ሥርዓት መደራጀታቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አሥራት አፀደወይን(ዶ/ር) ገለጹ።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የመጽሐፍት ዐውደ ርዕይ ''መጽሐፍት ለንባብ፣ ንባብ ለዕውቀት፣ ዕውቀት ለህይወት'' በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት ተጀምሯል።


 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አሥራት አፀደወይን(/) በዐውደ ርዕዩ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር የወጣቱን የንባብ ባህል ለማሳደግ አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ብለዋል።

ዲጂታል ቤተ-መጽሐፍትን ማስፋፋትና መጽሐፍትን ዲጂታላይዝድ ማድረግ ንባብን ለማበረታታትና አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ዩኒቨርሲቲው የዲጂታል ቤተ-መጽሐፍት በማቋቋምና ጥናታዊ ጽሁፎችና የተለያዩ መጽሐፍትን በዲጂታል ሥርዓት በማደራጀት አንባቢ ትውልድ አንዲፈጠር የድርሻውን እየተወጣ ነው ብለዋል።


 

እስካሁንም 400ሺህ በላይ የታሪክ፣ የሳይንስና የምርምር መጽሐፍትን ጨምሮ 10ሺህ በላይ የጥናት ውጤቶችን ወደ ዲጂታል በመቀየር ለተማሪዎች በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማሕበር ፕሬዝዳንት የዝና ወርቁ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የንባብ ባህልን ለማሳደግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና የጎላ ነው ብለዋል።

ተቋማቱ ወጣቱ መጽሐፍትን በቀላሉ ማግኘት የሚችልባቸው ዲጂታል አሰራሮች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸውም አንስተዋል።

ለአንድ ሳምንት በሚቆየው የመጽሐፍት ዐውደ ርዕይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ደራሲያን፣ አሳታሚዎችና መጽሐፍት አከፋፋዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም