ቀጥታ፡

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ለኢትዮጵያ እና ዛምቢያ አዳዲስ የኢንዱስትሪ እና ንግድ እድሎችን ይዞ መጥቷል - አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ

አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦‎ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ኢትዮጵያ እና ዛምቢያ የኢንዱስትሪና ንግድ ትብብራቸውን የበለጠ ማስፋት የሚችሉበትን ሰፊ እድል መፍጠሩን አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ ገለጹ።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት እ.አ.አ በ2018 በሩዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ልዩ ስብሰባ ላይ 54 የአፍሪካ ሀገራት ፈርመዋል።

ስምምነቱን ወደ ስራ ለማስገባት 22 ሀገራት በሀገራቸው ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ማስፀደቅ ይጠበቅባቸው የነበረ ሲሆን በወቅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ 31 ሀገራት በማጽደቃቸው ስምምነቱ ከታህሳስ 2013 ዓ.ም አንስቶ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል።


 

አሁን ላይ 48 ሀገራት ስምምነቱን በየሀገሮቻቸው ምክር ቤት አጽድቀዋል።

በኢትዮጵያ የዛምቢያ አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ህዝብ በሚኖርባት አህጉር ነጠላ ገበያን በመፍጠር ሰፊ እድሎችን ይዞ መምጣቱን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ዛምቢያ ስምምነቱን ፈርመው በህግ አውጪ ምክር ቤቶቻቸው ካጸደቁ ሀገራት መካከል እንደሚገኙበትም ጠቅሰዋል።

ይህም ሁለቱ ሀገራት በቀላሉ እንዲገበያዩ፣ ኢንዱስትሪዎችን እንዲያስፋፉና ምርቶቻቸውን በአፍሪካ ገበያ እንዲሸጡ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ተናግረዋል።

ሀገራቱ በአህጉራዊው ማዕቀፍ አማካኝነት ከሁለትዮሽ ትብብር ባሻገር ቀጣናዊ ትስስርን እውን ለማድረግ መስራት ይገባቸዋል ነው ያሉት።


 

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የሀገር ውስጥ ገበያ ፍላጎትን ለማሟላት ብቻ ሲሰሩ መቆየታቸው አቅማቸው እንዲገደብ አድርጓል።

ኢትዮጵያ እና ዛምቢያን ጨምሮ የሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የንግድ ማህበረሰቦች ያላቸውን ሀብት በማቀናጀትና በጋራ ማምረት ከቻሉ ከራሳቸው አልፈው ለአፍሪካ ገበያ የሚበቁ ምርቶችን ማቅረብ እንደሚቻል ነው የገለጹት።

የአፍሪካ ሀገራት የጋራ የምርት አቅም በመገንባትና የድንበር ተሻጋሪ ንግድን በማጠናከር ለኢኮኖሚ ትስስር እና ለተቀናጀ የጉምሩክ አሰራር ስርዓት እውን መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

በተጨማሪም ሀገራት ከአፍሪካ ውጪ የሚገኙ ምርቶች ላይ ተመሳሳይ መጠን ያለው ታክስ በመጣልና በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ማዕቀፍ በጋራ በመስራት የአፍሪካን ንግድ መጠበቅና ኢኮኖሚያቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ነጻ የንግድ ቀጣናው ለአፍሪካ ኢንዱስትሪ፣ የኢኮኖሚ እድገት እና እየተቀየረ ባለው የዓለም ስርዓት ውስጥ አፍሪካ ጠንካራ ሚና እንዲኖራት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና በያዛቸው ሀገራት ብዛት በዓለም ትልቁ የንግድ ቀጣና የሚያደርገው ሲሆን 54ቱ ሀገራት አሁን ያላቸው አጠቃላይ የምርት መጠን 3 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።


 

ነጻ የንግድ ቀጣናው የአፍሪካ ሀገራትን የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጥ ከማሳደግ ባለፈ የኤክስፖርት አቅማቸውን በማጎልበት ለኢኮኖሚ እድገታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የዓለም ባንክ ባስቀመጠው ስሌት የነጻ ንግድ ቀጣናው ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ከሆነ 30 ሚሊየን አፍሪካውያንን ከከፋ ድህነት፤ 70 ሚሊየን የአህጉሪቱ ዜጎችን ደግሞ ከመካከለኛ ድህነት ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ እና ዛምቢያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.አ.አ በ1965 መጀመራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም