በአማራ ክልል 293 ሺህ ሔክታር መሬት በበልግ ወቅት ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል 293 ሺህ ሔክታር መሬት በበልግ ወቅት ይለማል
ባሕር ዳር፤ ጥር 15/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በዘንድሮው የበልግ ወቅት 293 ሺህ ሔክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች እንደሚለማ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በልግ አብቃይ በሆኑ የሰሜን ሸዋ፣ ደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች 293 ሺህ ሔክታር መሬት በማልማት ከ5 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን በቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግም 4 ሺህ 226 ኩንታል ምርጥ ዘር እና ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እንደሚሠራጭ ለኢዜአ ገልጸዋል።
አርሶ አደሩም ዝናብን በማሳው ውስጥ ለማስቀረት የውኃ ማስረጊያ ስትራክሮችንና የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ እንዲያዘጋጅ እየተደረገ ነው ብለዋል።
አነስተኛ የበልግ ዝናብ ባለባቸው አካባቢዎች ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎችን ማልማት እንዲቻል እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የበልግ ዝናብ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች መዝነብ መጀመሩን ጠቁመው፤ ከተያዘው ጥር ወር መጨረሻ ጀምሮ የዘር ሥራ እንደሚካሄድ አመላክተዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን የደሴ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደሮች አሕመድ ሙሄ እና የሱፍ ሀሰን እንዳሉት፤ ግማሽ ሔክታር መሬታቸውን በበልግ ወቅት በገብስና በስንዴ ለማልማት የእርሻ ሥራ ጀምረዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግም ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ ለማለስለስና የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።