የተፋሰስ ልማት ሥራ የመሬት ለምነትን በመጨመር ምርታማነትን አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
የተፋሰስ ልማት ሥራ የመሬት ለምነትን በመጨመር ምርታማነትን አሳድጓል
ሃዋሳ፤ ጥር 15/2018 (ኢዜአ):-የተፋሰስ ልማት ሥራ የአፈር መሸርሸርን በማስቀረትና የመሬት ለምነትን በመጨመር ምርታማነታቸውን በማሳደጉ ልማቱን አጠናክረው መቀጠላቸውን የሲዳማ ክልል አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡
አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ እንዳሉት ቀደም ሲል በተፋሰስ ልማት ያከናወኗቸው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የአፈር መሸርሸርን በማስቅረትና የመሬት ለምነትን በመጨመር ምርትና ምርታማነታቸውን እያሳደገው ነው።
ተጠቃሚነታቸውን አጠናክሮ ለማስቀጠልም በአሁኑ ወቅትም የተፋሰስ ልማት ስራ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ከአርሶ አደሮቹ መካከል አቶ ቶማስ መራሳ እንደገለጹት በየዓመቱ በተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ በመሳተፍ የአካባቢያቸውን ለምነት እየጠበቁ ነው፡፡
ተፋሰስ ልማቱ ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚ እያደረጋቸው በመምጣቱ በአሁኑ ወቅትም በቡድን ተደራጅተው ልማቱን እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተከናውኖ ባገገሙ መሬቶችም ቡናና ፍራፍሬዎችን በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ሌላው አርሶ አደር ጴጥሮስ ሶቾሳ በበኩላቸው በተፋሰስ ልማት ሥራው አርሶ አደሩ በንቃት እየተሳተፈና ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
በአካባቢያቸው ከዚህ ቀደም ገላጣ የነበሩና የተጎዱ መሬቶች ማገገማቸውን ጠቅሰው፣ በእርሻ ማሳቸው የነበረውን ባህር ዛፍም በመንቀል የመሬታቸውን ለምነት እየጠበቁና ምርታማነት እያሳደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
የተፋሰስ ልማት ሥራው ምርት የማይሰጡ መሬቶች ወደ ምርት እንዲገቡና የሥራ እድል እንዲፈጠር ማድረጉን የገለጹት ደግሞ ሌላው አርሶ አደር ሳሙኤል ጢሞቲዮስ ናቸው።
ቀበሌያቸው ተዳፋታማ በመሆኑ ጎርፍ መሬታቸውን በመሸርሸር ለምነቱን እያጣ በመምጣቱ ከልማቱ ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከተጀመረ ወዲህ በየዓመቱ ምርታማነታቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው በክልሉ በየዓመቱ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የተጎዳ መሬት እንዲያገግም ጉልህ አስተዋጾ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የውሃ አማራጮችን በመጨመር የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና በመጫወታቸው ልማቱ በየዓመቱ እየተጠናከረ መምጣቱንም ገልጸዋል።
በዚህም በክልሉ በየጊዜው በሚካሄዱ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ የሚሳተፉ አርሶ አደሮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በዘንድሮ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ ከ147 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚለማ ሲሆን በተለዩ 678 ንኡስ ተፋሰሶች ለ30 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን ታውቋል።