በኦሮሚያ ክልል በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋ የፍትሕ አገልግሎት እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋ የፍትሕ አገልግሎት እየተሰጠ ነው
አዳማ፤ ጥር 15/2018 (ኢዜአ)፡- የፍትሕ አገልግሎቱን ቀልጣፋ፣ ግልጽና ተደራሽ የሚያደርግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራር እየተተገበረ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ኃላፊ ጉዮ ዋሪዮ ተናገሩ።
አዳዲስ የዲጂታል አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ዘመናዊና ቀልጣፋ አሠራር መዘርጋቱን ኃላፊው ገልጸዋል።
በዚህም ተገልጋዮች ያለ እንግልት ፍትሕ የሚያገኙበት ምኅዳር መፈጠሩንና የአገልግሎት መዘግየትም መቀረፉን ለኢዜአ አረጋግጠዋል።
የክስ መዝገቦችን ወደ ዲጂታል በመቀየር አገልግሎቱን በኦንላይን መስጠት መቻሉን፤ ምስክሮችን መጥራት ሳያስፈልግ በዞኖች፣ ከተሞችና ወረዳዎች የፍትሕ ጽሕፈት ቤቶች ቃላቸውን እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም የፍትሕ አገልግሎቱን ቀልጣፋ፣ ግልጽና ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፤ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ፖሊስና ዐቃቤ ሕጎች በትብብር የምርመራ መዝገቦችን የማጣራትና ክስ የመመስረት ሥራ እየሠሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህን ተከትሎም የመዝገብ ማጥራት ዐቅም እየጨመረ መምጣቱንና የክስ መዝገቦች የጥፋተኝነት ውሳኔ የማሰጠት ዐቅም እያደገ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
የፍትሕ አሰጣጥና አገልግሎት ተደራሽነት መጓተትና የጥራት ጉድለት ተሻሽሏል ሲሉም ተናግረዋል።
በገጠርና በከተሞች በሌብነት የተመዘበረ መሬትን በማስመለስና ሕገ ወጥ አሠራርን ከመከላከል አንፃር ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውንም አንስተዋል።
ለበርካታ አገልግሎት ሊውሉ የነበሩ ሕገ ወጥ የመሬት ካርታዎች እንዲመክኑ መደረጉንም ጠቁመዋል።