ቀጥታ፡

የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦትን ለማሳለጥ ከመንግስት ተግባር ጎን ለጎን የህዝብና የአጋር አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦ የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦትን ለማሳለጥ ከመንግስት ተግባር ጎን ለጎን የህዝብና የአጋር አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ገለጹ።

በውጭ አገር የሚኖሩ የቦረና ተወላጆች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለሞያሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የህክምና መስጫ ቁሳቁስ ድጋፍ ርክክብ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በዚሁ ወቅት፤ በጤና ተቋማት የሕክምና ግብዓቶችን እና ቁሳቁስ ለማሏላት ከሚከናወኑ ተግባራት ጎን ለጎን የአጋር አካላት ተሳትፎ ለተሳለጠ የህክምና አገልግሎት ዓይነተኛ ሚና አለው።


 

በሞያሌ ሆስፒታል የታየው የአካባቢው ተወላጆች ተሳትፎ መንግስት የሚሰራውን ስራ የሚያግዝ መሆኑን  አመልክተው፤ ለሌሎች አካባቢዎችም እንደ አርአያ የሚወሰድ በጎ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከሚኒሶታ የመጡት የድጋፉ አስተባባሪ ዶክተር አብዱራህማን ሮኔ እና ከአትላንታ ጆርጂያ የመጡት ዶክተር ዋቆ ዳደቻ የተደረገው ድጋፍ የመንግስትን ጥረት በአጅጉ የሚያግዝ ብሎም ለሆስፒታሉ ተጠቃሚዎች እፎይታን የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡  

ድጋፉ ከስዊድን ሂውማን ብሪጅ ከተገኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር የተመቻቸ መሆኑን ጠቅሰው፤  ከዚህ ቀደምም በቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ ለሚገኘው ተልተሌ ሆስፒታል እና በሜጋ ከተማ ለሚገኘው ሜጋ ሆስፒታል ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡


 

በቀጣይም ለአሬሮ እና ሌሎች ሆስፒታሎች ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ ማቀዳቸውን ጠቁመዋል።

የሞያሌ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አብዲ ኤደን፤ ሆስፒታሉ ለበርካታ ሰዎች አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ የተደረገው ድጋፍ በቀጣይ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ያግዘዋል ብለዋል። 

ይህ ተሳትፎ በሌሎች የልማት ስራዎች ላይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው የገለጹት፡፡


 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል ለተጨማሪ ህክምና ረጅም ርቀት ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር አንስተው፤ የተደረገው ድጋፍ እፎይታን የሚሰጥ እና እንግልትን የሚቀንስ በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም