ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመኸር እርሻ ከለማው ሰብል እስከአሁን 37 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል

አሶሳ፤ ጥር  15/2018(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመኸር እርሻ ከለማው ሰብል እስከአሁን 37 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰፊ ለም መሬትና በቂ የውሃ አማራጮች ያሉት ቢሆንም ባለው የተፈጥሮ ሀብት ልክ ታርሶ ለህብረተሰቡ ጥቅም ሳይውል ቆይቷል።

ከለውጡ ዓመታት ወዲህ ግን አርሶ አደሩ እና ከፊል አርሶ አደሩ ያለውን መሬት በስፋት እንዲያርስ የክልሉ መንግሥት ሰፊ ስራ እየሰራ ይገኛል።

በዚህም በተገኘው መነቃቃት ከክልሉ ነዋሪ ባለፈ ባለሀብቶችም በክልሉ በስፋት በግብርና ስራው በመሰማራታቸው ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ባበክር ሀሊፋ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ በክልሉ ከመኸር እርሻው በተጓዳኝ የበጋ ስንዴ የመስኖ ልማትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ሰብሎች በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ እየተመረተ ይገኛል።  

በዚህም በክልሉ በመኸር እርሻ ከለማው 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር ማሳ ላይ በተካሄደው የቅደመ ምርት ጥናት 54 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ  ተገምቷል።

እስከአሁን ድረስም ከተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ከ37 ሚሊየን 511 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

ከተሰበሰበው ምርት ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚሆነው ከበቆሎ እና ማሽላ ሰብል የተገኘ ምርት እንደሆነም ተናግረዋል።

በክልሉ የምርት አሰባሰብ ሂደቱ መቀጠሉን ገልፀው፥ በተለይም ከ137 ሺህ ሄክታር በላይ በማሽላ የለማ ማሳን ጨምሮ ሌሎች የሰብል ዓይነቶች እየተሰበሰቡ በመሆኑ ዕቅዱ እንደሚሳካ አመላክተዋል። 

የምርት ብክነት እንዳይከሰትም አርሶአደሩ ሰብልን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲሰበሰብ መደረጉን ተናግረዋል።

አርሶአደሩ የኩታገጠም እርሻ የሚያስገኘውን ዘርፈ ብዙ ጠቃሜታ በመገንዘብ እንዲሁም የግብርና ሜካናይዜሽን በስፋት ማከናወኑን አብራርተዋል።

በክልሉ የቅባት እህሎች ምርትም በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት አቶ ባበክር፤ ከ300 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ የለማ ሰሊጥ እና አኩሪአተር ምርት መሰብሰቡን እና ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ መቅረቡን አንስተዋል።

አርሶ አደሩ ከመኸር እርሻ በተጨማሪ በመስኖ ልማት አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ውጤታማ የግብርና ስራ እያከናወነ እንደሆነ አክለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም