ቀጥታ፡

አዲስ አበባ እያስመዘገበች የምትገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ ለአፍሪካ ከተሞች ተምሳሌት የሚሆን ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2018(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ከተማ እያስመዘገበች የምትገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ ለአፍሪካ ከተሞች ተምሳሌት የሚሆን ነው ሲሉ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከተሞች ከንቲባዎች ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ የልማትና የገቢ አሰባሰብ እንቅስቃሴ ላይ ያላቸውን አድናቆትም ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የአሕጉራዊ የተሞክሮ ልውውጥ እና የድርጊት መርሃ-ግብር ግምገማ አውደ ጥናት ተጠናቅቋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የተሳተፉ የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎችና የስራ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ያለውን የልማት እንቅስቃሴና የዲጂታል የገቢ አሰባሰብ ስርዓት ተመልክተዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከተሞች ከንቲባዎች ጋር በመሆን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ሀገራት ከተሞች ከንቲባዎች የከተማዋን የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ተሳታፊዎቹ በጉብኝታቸው ወቅት በአዲስ አበባ የታዘቧቸው ተሞክሮዎች ለሀገሮቻቸው ትልቅ ትምህርት የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የታንዛንያ ዳሬሰላም ከተማ ከንቲባ ኑረዲን ቢላለ፤ አዲስ አበባ ከተማ ራሷን በራሷ ለማስተዳደር የምታደርገውን ጥረት አድንቀው፤ ስለ አዲስ አበባ ከተማ አሁን በቂ ግንዛቤ አግኝቻለሁ ብለዋል።

ከተማዋ ግብር የምትሰበስብበትንና ተግባራትን የምታከናውንበትን መንገድ መመልከታቸውን ጠቅሰው ከዚህም ሰፊ ልምድ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ያገኙትን ተሞክሮዎች በዳሬሰላም ተግባራዊ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡


 

የሉሳካ ከንቲባ ቺላንዶ ቺታንጋላ አንዲት ከተማ ስኬታማ ለመሆን ጠንካራ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት ሊኖራት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በአዲስ አበባ ያየነው የገቢ አሰባሰብ ስርዓትና ገቢ እንዳይባክን የሚደረጉ የፈጠራ ስራዎች የሚደነቁ ናቸው ከዚህም ብዙ ልምድ ቀስመናል ብለዋል።


 

የካሜሩን ያወንዴ ከተማ የበጀት ቢሮ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሞዉጎ ብረቲንደ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ የተመለከቱት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ድንቅ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

በተለይም በገቢ አሰባሰብ በኩል የተመለከቱት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በካሜሩን ሊተገበር የሚገባው ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም