የሥነ ምድር ተመራማሪው ጤናዓለም አየነው(ፕ/ር) ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ - ኢዜአ አማርኛ
የሥነ ምድር ተመራማሪው ጤናዓለም አየነው(ፕ/ር) ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ምዘና ሳይንስ ኮሌጅ የሥነ ምድር ትምህርት ክፍል መምህር እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሥነ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ ሳይንቲስት የሆኑት ጤናዓለም አየነው (ፕ/ር) በዛሬው ዕለት ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ጤናዓለም አየነው (ፕ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ30 ዓመታት በላይ ከማስተማር ባለፈ በዓለም አቀፍ የሥነ ምድር እና ከርሰ ምድር ውሃ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
የከርሰ ምድር ውሃ ላይ ሰፊ እና ጥልቅ ምርምር በማካሄድ የሚታወቁ ሲሆን ከ2 ሺህ በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታተሙ የምርምር ሥራዎች ባለቤት ናቸው።
ለኢትዮጵያ በከርሰ ምድር የውሃ ዘርፍ ብዛት ያላቸው ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናታዊ ምርምሮችን በመስራት ቀዳሚ መሆናቸውንም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምድር ትምህርት ክፍል የከርሰ ምድር ውሃ ተመራማሪ ሚካኤል ጥላሁን (ፕ/ር)ተናግረዋል።
እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ ባስተማሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎቻቸው እንደ አባት መካሪ ለሙያ ባልደረቦቻቸው ደግሞ እንደ ወንድም አጋዥ እንደነበሩም አውስተዋል።
የበለስ ኢንጂነሪንግ መስራችና ባለቤት ጤናዓለም አየነው (ፕ/ር) ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነበሩ።
የጤናዓለም አየነው (ፕ/ር) ቀብር ሥነ ሥርዓት በነገው ዕለት ከቀኑ 9 ሰዓት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ፋና ዲጂታል ዘግቧል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጤናዓለም አየነው (ፕ/ር) ሕልፈት የተሰማውን ሐዘን ገልጾ ለቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸውና ተማሪዎቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።