አዋጆቹ ዓለም አቀፍ አሰራርን መሰረት ያደረጉና ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችሉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
አዋጆቹ ዓለም አቀፍ አሰራርን መሰረት ያደረጉና ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችሉ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2018(ኢዜአ)፦ ፍርደኞችን የማስተላለፍ እና የወንጀል ጉዳይ የአሳልፎ መስጠት አዋጆች ዓለም አቀፍ አሰራርን መሰረት ያደረጉና ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችሉ መሆናቸውን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ ገለጹ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 9ኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ተካሂዷል።
በምክር ቤቱ የህግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ እንደተናገሩት በኢትዮጵያና በሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና እንዲሁም በኢትዮጵያና በብራዚል ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግሥታት መካከል ፍርደኞችን የማስተላለፍ ስምምነቶች ተደርገዋል።
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ መንግሥታት መካከል በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት መደረጉንም ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሀገራቱ ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ፍርደኞችን የማስተላለፍና የወንጀል ጉዳይ አሳልፎ የመስጠት አዋጆችን መርምሮ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
አዋጆቹ ዓለም ዓቀፍ አሰራርን መሰረት ያደረጉ፣ የፍርደኞችን መብት ያከበሩና የማስተላለፉን ስነ-ስርዓት በመከተል የሚፈፀሙ ናቸው ብለዋል።
በተለይም ሀገራቱ የብሪክስ አባል ሀገራት በመሆናቸው ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አዋጆቹ ከሀገራቱ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክር ገልጸው፤ ከህግ ተፈጻሚነት አንጻር ጥያቄ አቅርበዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ የአዋጆቹ የህግ ተፈጻሚነት ላይ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሌላው ምክር ቤቱ በሶስት ረቂቅ አዋጆች ላይ የተወያየ ሲሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት ኃይሌ አዋጆቹን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታዋ በኢትዮጵያ አቪዬሽን ሴኩዩሪቲ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ፣ የፌዴራል የስፖርት ልማት፣ አስተዳደርና የሕብረት ሥራ ማሕበራት ረቂቅ አዋጆችን አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት እና በኮሪያ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ መካከል የሕክምና መሳሪያ አቅርቦት ፕሮጀክት ምዕራፍ-2 ማስፈፀሚያ የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅንም አቅርበዋል።
አዋጆቹ ከሀገራቱ ጋር ያለውን ንግድና ኢንቨስትመንት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ በቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ላይ ውይይት በማድረግ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷቸዋል።