የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የውስጥና የውጭ የስጋት ኃይሎችን እንቅስቃሴዎች የሚቀለብሱ ስምሪቶች አከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የውስጥና የውጭ የስጋት ኃይሎችን እንቅስቃሴዎች የሚቀለብሱ ስምሪቶች አከናውኗል
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2018 (ኢዜአ)፦ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የውስጥና የውጭ የስጋት ኃይሎችን እንቅስቃሴዎች የሚቀለብሱ ስምሪቶች ማከናወኑን አስታወቀ ።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የ2018 የመጀመሪያ ግማሽ በጀት አመት ዕቅድ አፈጻጻም ግምገማዊ ውይይት የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ስትራቴጂክ አመራሮች በተገኙበት ተካሂዷል።
በመድረኩም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በ2018 በጀት ዓመት አስቀምጧቸው የነበሩ ሀገራዊ የጸጥታ ሁኔታን የማጽናት፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምረቃን ጨምሮ የአደባባይ ክብረ በዓላት እንዲሁም ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ኹነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ የማድረግ፤ የተቋማዊ የሪፎም አጀንዳዎችን የመከለስና ለሀገራዊ ምርጫው ስኬት የሚረዱ ዝግጅቶች በላቀ ደረጃ የተፈጸሙ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡
ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመሆን በተከናወኑ ስምሪቶች በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የስጋት ኃይሎችን በማዳከም ረገድ መሰረታዊ ለውጥ የተመዘገበ መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
በተሳሳተ መንገድ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂ ኃይሎች ከሕግ ማስከበር አማራጭ ጎን ለጎን መንግሥት በሚያቀርበው የሰላም ጥሪ አማካኝነት ትጥቅ እየፈቱ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ የሚረዱ ስምሪቶች መከናወናቸውም በስኬትነት ተነስቷል፡፡
በውጭ ሀገር የመረጃ ስምሪት በተከናወኑ ስር-ነቀል የለውጥ ሥራዎች በሀገራዊ ጥቅምና ደኅንነት ላይ የሚቃጡ ስጋቶችን መቀልበስና መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀም መቻሉ የተገለጸ ሲሆን፤ በዓለምአቀፋዊና ቀጣናዊ ተለዋዋጭ የደኅንነት ምህዳር ውስጥ የኢትዮጵያን ከፍታና የሕዝቦቿን ተጠቃሚነት የሚያረጋገግጡ ስትራቴጂክ ድሎች እየተመዘገቡ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በግማሽ የበጀት ዓመቱ ተቋሙ የተሰጡትን የመረጃ፣ የደኅንነትና የሥነ-ልቦና ጦርነት የተልዕኮ ሥራዎች በላቀ መንገድ የመፈጸም አቅሙ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉም ተመልክቷል፡፡
በዚህም ስጋቶችን ከመቀልበስ ባሻገር ቀድሞ ችግሮችን በመለየትና አዝማሚያዎችን በመተንተን ድንገተኛ የሚባሉ የደኅንነትና የፀጥታ ክፍተቶችን ማስቀረት መቻሉ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
አሁንም ሰላምና ፀጥታ የማጽናት ሂደቱ ያልተዋጠላቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች የፈጠሩት ግንባር እንዲሁም ቀጣናውን የኃይል አሰላለፍ ፍጥጫ በማድረግ ረገድ የሚታዩት እንቅስቃሴዎች ተግዳሮቶች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡
ይህን የሚቀለብስ ተቋማዊ ዝግጁነት መገንባቱም ተገልጿል፡፡
በተቋሙ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ተልዕኮን በላቀ ደረጃ ለመፈጸም መሰረት መሆናቸውን የጠቀሰው መግለጫው፤ ወቅታዊና የመጪውን ዘመን የደኅንነት ስጋቶች ታሳቢ ባደረገ መልኩ አዳዲስ የሪፎርም አጀንዳዎች በመቅረጽ ውጤታማ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አብራርቷል፡፡
አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ባለፉት ስድስት ወራት ሀገራችን በ2018 የምታካሄደው 7ኛ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫን ታሳቢ በማድረግ እቅድ አውጥቶ ሲዘጋጅ መቆየቱ በግምገማው ተጠቅሷል፡፡
ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት በምርጫ ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የስጋት ምንጮችን ለመለየት የዳሰሳ ጥናት አካሂዷል፡፡
በዳሰሳ ጥናት የተለዩ ስጋቶችን ለመቀልበስ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ፣ በስልጠናና በሥነ-ልቦና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በመግለጫው፤ በሚቀጥሉት ወራት የሚከናወኑት የአፍሪካ ህብረት ጉባኤና ሌሎች ትላልቅ ኹነቶች እንዲሁም ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ያለአንዳች የፀጥታ ችግር እንዲከናወኑ በተሟላ የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂና የሎጀስቲክስ ቁመና ላይ እንደሚገኝ በግምገማዊ ውይይት መድረክ መገለጹን አስታውቋል።