በጀጎል አለም አቀፍ ቅርስ ውስጥ እየተሰሩ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች ትውልዱ በታሪክ እንዲታወስ የሚያደርጉ ናቸው - አቶ ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
በጀጎል አለም አቀፍ ቅርስ ውስጥ እየተሰሩ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች ትውልዱ በታሪክ እንዲታወስ የሚያደርጉ ናቸው - አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2018(ኢዜአ)፦ በጀጎል አለም አቀፍ ቅርስ ውስጥ እየተሰሩ የሚገኙ የኮሪደርና የመልሶ ማልማት ስራዎች እንደ አባቶች ሁሉ ትውልዱ በታሪክ እንዲታወስ የሚያደርጉ ናቸው ሲሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በጀጎል አለም አቀፍ ቅርስ ውስጥ በተለያዩ ስፍራዎች እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደርና የመልሶ ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በዚህ ወቅትም ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት በተለይም በአንደኛ መንገድ፣ በጊዲር መጋላ፣ በጀጎልና በሌሎች ዋና ዋና መንገዶች ውጤታማ የኮሪደርና የመልሶ ልማት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
የመስክ ምልከታውም ከዚህ ቀደም የተሰጡ ግብረ መልሶች ተግባራዊ ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም አብዛኞቹ ስራዎች ጥራትን፣ ፍጥነትንና ፈጠራን መሰረት ባደረገ መልኩ እየተሰሩ መሆናቸውን ተመልክተናል ብለዋል።
አንዱ የኢትዮጵያ መልክ የሆነውና በአለም ቅርስነት በተመዘገበው የጀጎል ቅርስ ውስጥ የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በቅርሱ ላይ ከተጋረጠው አደጋ በመታደግ የአለም አቀፍ ቅርስነቱን ጠብቆ እንዲቆይ ከማስቻል ባሻገር እንደ አባቶች ሁሉ ትውልዱ በሌላ ገድል እንዲታወስ የሚያደርጉ ናቸው።
ስራዎቹም የጀጎል ቅርስን የአለም አቀፍ ህያው ሃብት ከመሆን በተጨማሪ የሀገር ውበትና መገለጫነቱን የሚያጎሉ ናቸው ሲሉ ነው የተናገሩት።
እየተከናወኑ በሚገኙ ስራዎችም የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ስለመሆኑ ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም የተጀመሩ ስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ይሰራል ብለዋል።