ቀጥታ፡

በክልሉ 5ኛው ክልል አቀፍ የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫልና የስፖርት ውድድር መካሄድ ጀመረ

ቦንጋ፤ ጥር 14/2018(ኢዜአ)፦ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 5ኛው ክልል አቀፍ የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫልና ልዩ ልዩ ስፖርቶች ውድድር በቦንጋ ከተማ መካሄድ ጀመረ።

ውድድሩ "ስፖርታችን ለኢትዮጵያ እድገት ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ ከጥር 14 እስከ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ ታውቋል።


 

በውድድሩ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በክልሉ በሀገርና በዓለም መድረክ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በትኩረት መስራት ይገባል።

ውድድሩ በአዕምሮና በአካል ብቁ ዜጋ ለማፍራት ካለው ፋይዳ ባሻገር ሀገርን ወክለው በዓለም አደባባይ የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ጭምር ለማፍራት ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

ለዚህም በየአካባቢው ለወጣቶች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር መስራት እንደሚገባ ጠቁመው የክልሉ መንግስትም የስፖርት ዘርፉን ለማገዝ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ፌስቲቫሉና ውድድሩ በተለይም ተዘንግተው የቆዩ የባህል ስፖርቶችን አውጥቶ ለትውልድ ከማስተላለፍና የእርስ በርስ ትስስርን ከማጠናከር አንጻር ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።


 

የክልሉ  ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ ፋንታሁን ብላቴ በበኩላቸው ስፖርት ለህዝቦች ትስስርና አንድነት መጠናከር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት የሚካሄደው ውድድር ታዳጊ ስፖርተኞች የሚመለመሉበትና የባህል ልውውጥ የማደረግበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ውድድሩ በ11 የስፖርት ዓይነቶች የሚካሄድ ሲሆን በታዳጊ ወጣቶች ምዘና ውድድር ላይ የሚሳተፉ ብቁ ስፖርተኞችም እንደሚመለመሉ ታውቋል።

በውድድሩ ቤንች ሸኮ ዞን ከምዕራብ ኦሞ ዞን ባደረጉት የእግር ኳስ ውድድር የተጀመረ ሲሆን፣ ከክልሉ ሁሉም ዞኖች የተውጣጡ ከ600 በላይ ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም