ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የከተሞች ትራንስፎርሜሽንን የልማት እቅዷ ማዕከል ማድረጓ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርአያ የሚሆን ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የከተሞች ትራንስፎርሜሽንን የልማት እቅዷ ማዕከል ማድረጓ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርአያ የሚሆን ነው ሲሉ የቢግ ዊን ፊላንትሮፒ የከተሞች ከፍተኛ ዳይሬክተር ሄስቲንግስ ቺኮኮ ገለጹ፡፡ 

የኢትዮጵያን የከተሞች የትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለማፋጠንና የከተሞችን የሀብት ማሰባሰብ አቅም ማሳደግ የሚያስችል ስልታዊ ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ ተቋም ቢግ ዊን ፊላንትሮፒ (Big Win Philanthropy) ጋር በይፋ ተፈራርመዋል።


 

የቢግ ዊን ፊላንትሮፒ የከተሞች ከፍተኛ ዳይሬክተር ሄስቲንግስ ቺኮኮ በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የከተሞችን ትራንስፎርሜሽን የልማት እቅዷ ማዕከል ማድረጓ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ አርአያነት ያለው ተግባር ነው።

ኢትዮጵያ የከተሜነትን ሂደት በታቀደ ስልት እና በጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እየመራች መሆኑ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በከተሞች ስኬት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቁመው፤ ከተሞች ለዜጎቻቸው ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ምርታማነትን ማሳደግ፣ ጥራት ያለው መሠረተ ልማት ማቅረብ እንዲሁም ፍትሐዊና ተደራሽ አገልግሎቶችን ማረጋገጥ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡  

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የያዘችው ጠንካራ የለውጥ መርሃ ግብር ውጤታማ እንዲሆን ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል፡፡ 

ይህ አዲስ የተፈረመው ስምምነት የሀብት ማሰባሰብ፣ የፋይናንስ አስተዳደር እንዲሁም የትራንስፎርሜሽን ጉዞውን ማፋጠን በሚሉ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም