የኢትዮጵያና የጀርመን የፖለቲካ የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የጀርመን የፖለቲካ የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና በጀርመን መካከል ያለው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለፁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከጀርመን ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆአን ዋድፉልን ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ውይይቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ እና ጀርመን የቆየና ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው ብለዋል፡፡
ሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት በ2018 ዓ.ም የሚያከብሩበት ልዩ ዓመት መሆኑን ጠቅሰው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት ይበልጥ ለማሳደግ ከስምምነት መደረሱን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የጀርመን ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ በቡድን 20 (G-20) መሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ያደረጉት ስብሰባ የላቀ አጋርነትና መነቃቃትን የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት የዚሁ ፍላጎት ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት ውይይት የሁለትዮሽ የፖለቲካ ምክክርና የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽንን ጨምሮ ነባር የሁለትዮሽ አሰራሮችን በድጋሚ ለማስጀመር ከስምምነት መደረሱን ጠቅሰዋል።
በውይይታቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር መግባባት ላይ መደረሱን አስታውሰዋል።
የጀርመን ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆአን ዋድፉልን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እና ጀርመን ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳለቸው ጠቅሰው፤ ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ እንደምታጠናክር አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት ያደነቁት ሚኒስትሩ፤ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የጀርመን ኩባንያዎች በግንባታው ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል።
በዚህ የለውጥ ወቅት ግንኙነታችንን ማጠናከርና መጠበቅ ይኖርብናል ያሉት ሚኒስትሩ የ120 ዓመታት የዲፕሎማሲ ታሪክ ለዚህ ጠንካራ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።