በጤናው ሴክተር የተያዙ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው - ዶክተር ደረጀ ዱጉማ - ኢዜአ አማርኛ
በጤናው ሴክተር የተያዙ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው - ዶክተር ደረጀ ዱጉማ
ሆሳዕና ፤ ጥር 14/2018 (ኢዜአ) :- በኢትዮጵያ በጤናው ሴክተር የተያዙ ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለፁ፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጤናውን ዘርፍ ለማጠናከር ያለመ "ጠንካራ የአመራር ስርዓት ግንባታ ለውጤታማ የጤና ስርዓት" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ስልጠና በሆሳዕና ከተማ እየተሰጠ ነው፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጀ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በጤናዉ ሴክተር የተያዙ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት ጠንካራ አመራር መገንባት ይገባል፡፡
የልማት አጀንዳዎችን ተፈጻሚ በማድረግና ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ መፍጠር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አመራሩ ማህበረሰቡን በማስተባበር በሴክተሩ እመርታዊ ለውጥ እንዲመዘገብ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዲጅታል ቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎቶችን ማስፋት፣ የጤና ተቋማትን ደረጃ ማሻሻልና የተሟላ ግብዓት ማቅረብ ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማጠናከር ታስበው የተከናወኑና ተጠናክረው የሚቀጥሉ ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በበኩላቸው የማህበረሰቡን የጤና ችግር መቅረፍ የሚችሉ ጠንካራ አመራሮችን መፍጠር የስልጠናው ዋና ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ቢሮው በጤናው ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት መቅረፍ የሚያስችል ጥናት ማካሄዱን አስታውሰው ስልጠናው የአመራሩን አቅም በመገንባት መፍትሄ ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ወቅቱ የደረሰበትን ደረጃ የሚመጥን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የጤና አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማሳካት ስልጠናው ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ማህበረሰቡን በማስተባበር በቅንጅት እየተከናወኑ ያሉ የጤና ተቋማት ግንባታና ግብአት የማሟላት ስራዎችን አጠናክሮ የማስቀጠል ስራም ይሰራል ነው ያሉት፡፡
ለሰባት ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው በዚሁ ስልጠና ከክልሉ ከተለያዩ መዋቅሮች የተውጣጡ ከ175 በላይ የጤናው ዘርፍ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡