ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የማር ምርታማነትን ለማሳደግ በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮች ተግባራዊ እያደረገች ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የማር ምርታማነትን ለማሳደግ በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮች ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ንብ ሀብት ማህበር እና የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(UNIDO) በንብ ሀብትና በማር ምርታማነት ዙሪያ የመከሩበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ የተገኙት የግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና አሳ ሀብት ዘርፍ የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ግርማ ሙሉጌታ እንደተናገሩት፤ የማር ሀብትን በውጤታማነት ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል የተሻሻለ አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል።

መንግስት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠው ልዩ ትኩረት መነቃቃት መፍጠሩን ገልጸው፤ አምራቾች በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን እንዲከተሉ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ጠቁመዋል።

ለዚህም ስኬት ከበለጸጉ ሀገራት ጋር የሚደረግ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር፣ የልምድ ልውውጥ ስራዎች እንዲሁም የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አብራርተዋል።

መድረኩ የማር ምርት ጥራትን በመጠበቅ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ምርት ለማሳደግና ዘላቂ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ጠቁመዋል።


 

በአፍሪካ ህብረት እና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(UNIDO) ተጠሪ ስቴፍን ካግቦ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው እድገት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለማቅረብ የተገነቡት ሶስት የተቀናጁ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለዘርፉ ትልቅ ተስፋ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እነዚህ ፓርኮች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸውና ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን በመሳብ በኩል ውጤታማ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በዘርፉ ስኬታማ ለመሆን ለሚፈልጉ ሌሎች ሀገራት እንደ ትልቅ የልምድ ምንጭ እያገለገሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በማር ምርት ዘርፍ የጀመረቻቸው ስራዎች ውጤታማ እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸው፤ የUNIDO እና የኢትዮጵያ መንግስት ቅንጅት ለሌሎች ሀገራትም አርአያ የሚሆን ተግባር ነው ብለዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ንብ ሀብት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ነጋሽ በቃና በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ማርን እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ በማቅረብ በኩል መንግስት ለዘርፉ ምርታማነት ያመቻቸውን የፖሊሲና የአሰራር ድጋፎች በአግባቡ ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ማህበሩ በመንግስትና በግል አጋርነት የሚከናወኑ ተግባራት እንዲጠናከሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ውይይቱ ለሀገሪቱ የማር ዘርፍ እድገት አዲስ አቅጣጫ ይጠቁማል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም