ኢትዮጵያ በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ አራተኛ ቀኑን በያዘው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በተመራው ልዑክ አማካኝነት የነቃ ተሳትፎ እያደረገች ትገኛለች።
ሚኒስትሩ የዓለም አቀፍ ጤና እና ፋይናንስ የወደፊት ዕጣ ፈንታን አስመልክቶም በቢልጌትስ አስተናጋጅነት ትላንት በተካሄደው ውይይት ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ሚኒስትሩ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂንና ሰው ሰራሽ አስተውሎት(AI) በመጠቀም፣ በተለይም በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍሎች የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት እያደረገች ያለውን እድገት አብራርተዋል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት(AI) እና የጤና ስርዓቶችን ለማጠናከር፣ የሰዉ ሃይል ልማትን ለማበረታታትና የዲጂታል መሰረተ ልማትን ለማሳደግ የረጅም ጊዜ አጋርነት እና ዘላቂ ፋይናንስ እንዲኖርም ጥሪ አቅርበዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ “ከድንገተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ባሻገር ያሉ ኢኮኖሚዎች” በሚለው የውይይት መድረክ ላይም ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት ለመገንባት የሚያስፈልጉ ቁልፍ አምዶችን ዘርዝረዋል፡፡
ከፎረሙ ጎን ለጎንም ከቢልጌትስ እና ከአውሮፓ ህብረት የዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ለፈጠራ፣ ለአጋርነት እና ለዘላቂ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም ያረጋገጠ ነው።
እስከ አሁን ያለው የኢትዮጵያ የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም 2026 ተሳትፎ፣ ሀገሪቱ ዘላቂና ሁሉን አቀፍ እድገት ለማምጣት ፈጠራን፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንንና ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ለመጠቀም ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑም ተገልጿል።