ቀጥታ፡

የጤና ባለሙያዎችን የማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮግራም ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2018(ኢዜአ)፦ በመንግስት ተቋማት የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችን የማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮግራም ይፋ ተደረገ።

የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ መንግስት ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የሚያስችሉ በርካታ ስትራቴጂዎችን በመተግበር ውጤታማ ስራ ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።

ተቋሙ ህጎችንና ደንቦችን መሰረት በማድረግ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ዜጎች በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከእነዚህ ህጎች መካከል በመንግስት ተቋማት የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችንና ቤተሰቦቻቸውን የማህበራዊ ጤና መድህን ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያዘው ድንጋጌ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመንግስት የጤና ተቋማት 492 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ እስካሁን 181 ሺህ የሚሆኑት የጤና ባለሙያዎች በኦንላይን መመዝገባቸውን አስታውቀዋል።

ማህበራዊ ጤናን ማረጋገጥ ከማህበራዊ ተግባራት ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰው፤ ምርታማና ጤናማ ዜጋን መፍጠር የሁል ጊዜ ተግባር ነው ብለዋል።

ዜጎችን የጤና መድህን ተጠቃሚ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም