በአፋር ክልል የሚገኙ የዴሞክራሲ ተቋማት ሃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት የሚያስችል አደረጃጀትና አሰራር ተግባራዊ እያደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የሚገኙ የዴሞክራሲ ተቋማት ሃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት የሚያስችል አደረጃጀትና አሰራር ተግባራዊ እያደረጉ ነው
ሰመራ፣ ጥር 14/2018(ኢዜአ) ፡-በአፋር ክልል የሚገኙ የዴሞክራሲ ተቋማት የተጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት መወጣት የሚያስችል አደረጃጀትና አሰራር ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለፀ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት በአፋር ክልል የሚገኙ የዴሞክራሲ ተቋማት ላይ የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
ምልከታ ከተደረገባቸው ተቋማት መከካከል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ይገኙበታል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እውነቴ አለነ በአፋር ክልል የሚገኙት የዴሞክራሲ ተቋማት አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ማሳየቱን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለይ የተቋማቱ ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፣ተቋማቱ የአሰራርና የአደረጃጀት ለውጦችን በማድረግ የተገልጋዩን እርካታ ለመጨመር የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀዋል።
የዴሞክራሲ ተቋማቱ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት መወጣት የሚያስችላቸውን አደረጃጀትና አሰራር ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑንም ነው ሰብሳቢው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የአፋር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን ለማከናወን በምርጫ ክልሎች አስፈፃሚዎችን ማደራጀቱና የምርጫ ጣቢያዎች አስፈጻሚዎች ምልመላ እያከናወነ መሆኑን መመልከታቸውን ነው ያነሱት።
የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምም በክልሉ የአስተዳደር በደሎችን አስቀድሞ ለመከላከል የጀመራቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን የበለጠ ሊያጠናከር ይገባል ብለዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባል አቡኔ ዓለም በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቅርንጫፎች መረጃን ተደራሽ በማድረግ የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው ብለዋል።
ኢዜአ በክልሉ የሚከናወኑ የልማትና የሰላም ግንባታ ሥራዎች ላይ ተከታታይ ዘገባ በመስራት ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ መሆኑንም አንስተዋል።
በሰመራ ከተማ እየተገነባ ያለው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ስቱዲዮን በሰው ሃይልና በግብአት ማሟላት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
የሚዲያ ተቋማቱ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ በመሆን የተጣለባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት እንዲተጉ አሳስበዋል።